Wednesday, September 20, 2017

በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚሰበሰው እርዳታ በቂ አይደለም ተባለ

(ኢሳት ዜና መስከረም 10 ቀን 2010 ዓም) በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚሰበሰው እርዳታ በቂ አይደለም ተባለ
የፖለቲካ መሪዎች ባስነሱት ግጭት የተነሳ ለተፈናቀሉ ከ50 ሺ በላይ ዜጎች የእለት እርዳታ የሚሆን ገንዘብ በተለያዩ ወገኖች እየተሰባሰ ቢሆንም፣ የእርዳታው መጠን ከችግሩ መጠን ጋር ሲነጻጻር እጅግ አነስተኛ ነው። በምስራቅ ሃረርጌ እና በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች ህዝቡ በቻለው አቅም እርዳታ በማሰባሰብ ልገሳ እያደረገ ሲሆን፣ እስካሁን እየተሰጠ ያለው እርዳታ ከተፈናቃዮች ቁጥር ጋር ሲተያይ እጅግ አነስተኛ ነው። በተለይ የእርዳታ ማሰባሰቡ ስራ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የሚደርሰው ጉዳትም ከፍተኛ ስለሚሆን፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የአለማቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ተፈናቃዮች ጠይቀዋል። ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን ቦታዎች ለመመልከት የቻለው ዘጋቢያችን፣ ሁኔታው እጅግ ከባድ መሆኑን ገልጿል። በተለይ ሃረር ሰፍረው በሚገኙ ተፈናቃዮች መሃል ከምግብ እጥረትና ከጽዳት ጋር በተያያዘ የኮሌራ በሽታ ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ማየሉን ገልጿል።

በአሁኑ ሰአት የመከላከያ ሰራዊት በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰፍሮ ቅኝት እያደረገ በመሆኑ ግጭቱ መቀነሱን የሚገልጸው ዘጋቢያችን፣ በግጭቱ ተሳትፈዋል እየተባሉ ሰዎች መያዛቸው ሌላ ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ነዋሪዎችን በማነጋገር ዘግቧል።
ተፈናቃዮች ወደ መጡበት የሶማሊ ክልል ይመለሳሉ የሚለው ተስፋ አነስተኛ ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ተፈናቃዮች ፣ ወደ መጡበት ክልል ከመመለስ ይልቅ የተሻለ ቦታ ተሰጥቷቸው ህይወታቸውን እንዲያቋቁሙ ይጠይቃሉ።

No comments:

Post a Comment