Monday, September 18, 2017

ደቡብ አሮምያ አዋሳኝ ቦታዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉት ዜጎች ተረስተዋል

(ኢሳት ዜና መስከረም 08 ቀን 2010 ዓም)በደቡብ አሮምያ አዋሳኝ ቦታዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉት ዜጎች ተረስተዋል
ከሃምሌ 16 ቀን 2009 ዓም በጉጂ ኦሮሞ ማህበረሰብ እና ደቡብ ክልክ አማሮ ወረዳ በሚገኘው ኮሬ ማህበረሰብ እንዲሁም በጉጂና በቡርጂ መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ እስከ 100 ሺ ዜጎች ተፈናቅለው በተለያዩ ተራራዎች ላይ ሰፍረው እንደሚገኙና ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደተጋለጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። እርዳታ የሚሰጣቸው አካል በመጥፋቱም ለችግር ተዳርገዋል። 
ግጭቱ ባለፈው ሳምንት እጅግ በመባባሱ ሁለት የፌደራል ፖሊሶችን ጨምሮ ከሁሉም ወገን ከ20 ያላነሱ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በርካታ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል። 
ግጭቱ ከገጠር አልፎ ወደ ከተሞችም በመዛመቱ አሁን ቡሌ ሆራ እተባለች በምትጠራው ሃገረ ማርያም ከተማ ካለፉት 4 ቀናት ጀምሮ ማንኛውንም የመንግስት ስራና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቋርጦ ቆይቷል። ህዝቡ ከቤቱ ሳይወጣ ለ4 ቀናት ያክል መቆየቱን ዛሬ አንዳንድ ድርጅቶች መከፈታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላት በብዛት በከተማዋ እንደሚታዩና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ የሚገለጹት ነዋሪዎች፣ እስካሁን ባለው መረጃ 6 የከተማው ሰዎች ተገድለዋል። በአካባቢው አሁንም ሰላም ሰፍኗል ለማለት እንደማይቻልና ውጥረት እንዳለም አክለው ገልጸዋል። በገጠር አካባቢ ያለው ሁኔታ ግን አሁንም አስከፊ ሆኖ ቀጥሎአል።
ግጭቱ የድንበር ማካለል እናደርጋለን በማለት የሄዱ ባለስልጣናት ለዘመናት ተከባብሮና ተዛምዶ የሚኖረውን ህዝብ እንዲጋጭ ማድረጋቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment