Tuesday, September 19, 2017

የሃረሪ ክልል ባለስልጣናት ሽጉጥ ተማዘዙ

የኦሮሞ ህዝብ በሃረሪ ክልል ባለስልጣናት የሚደርስበትን ጭቆና በመቃወም የተለያዩ ሰልፎችን ማድረጉን ተከትሎ፣ ከሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ጎን በመቆም በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ጭቆና እንዲባባስ አድርገዋል በሚል እንዲሁም በተለያዩ የዝርፊያ ወንጀሎች ሲወነጀሉ የቆዩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሃምዛ ሙሃመድ ከስልጣን መባረራቸውን ተከትሎ ፣ እርሳቸውን ለማስተዋወቅ በተጠራው ስብሰባ ላይ የፕሬዚዳንቱ ጠባቂ ሽጉጥ በማውጣት በኦህዴድ ባለስልጣናት ላይ ደቅኗል። 
። ግለሰቡ ከሁለት ሳምንት በፊት ኦህዴድ አዲስ አበባ ላይ ባደረገው ስብሰባ ላይ መነሳታቸውን ቀደም ብሎ መረጃው የደረሰን ሲሆን፣ ዛሬ በይፋ ከስልጣን መነሳታቸውንና በምትካቸው አቶ ጋቢሳ ተስፋዬ የሚባሉ ሰው መሾማቸውን እርሳቸውን ለማስተዋወቅ በተደረገ ዝግጅት ላይ ለማረጋገጥ ተችሎአል።
አዲሱን ምክትል ፕሬዚዳንት ለማስተዋወቅ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙራድ አብዱላሂ ጠርተውት በነበረው ስብሰባ ላይ፣ የክልሉ የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ምጄና እና የክልሉ የፍትህና ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊው አቶ ጀማል፣ “ አክራሪዎችና ክልሉን የሚበጠብጡ በመሆናቸው በዚህ ስብሰባ ላይ ሊገኙ አይገባቸውም” የሚል አቋም የያዙት ፕሬዚዳንቱ ፣ በቦታው የተገኙት ሁለቱ ባለስልጣናት ከስብሰባ እንዲወጡ ሲጠይቁ “አንወጣም” በማለታቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ጠባቂ ሽጉጥ መዝዞ እንዲወጡ ለማስፈራራት ሞክሯል። በዚህ ድርጊት የተበሳጩት አቶ አብዱማሊክም እንዲሁ ሽጉጣቸውን የመዘዙ ሲሆን፣ ጉዳዩ ወደ ደም መፋሰስ ሳያመራ በግልግል ተቋጭቷል። በሁኔታው የተበሳጩት አዲሱ ተሷሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ “ እነሱ በሌሉበት ስብሰባ አልሳተፍም” በማለት፣ የትውውቁን ዝግጅቱን ረግጠው ጥለው በመውጣት ስብሰባው ተበትኗል።


ከ3 ሳምንት በፊት የሐረሪ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ የኦህዴድ አመራሮችን እርሳቸውን ሳያስፈቅዱ ስብሰባ በመጥራታቸው እንደሚያስሩዋቸው በመዛታቸውና ኦህዴድንም እንደ ደርጅት እንደማያዩት በመናገራቸው ስብሰባውን ረግጠው የወጡት አቶ አለማየሁ ምጄናና አቶ ጀማል ፣ በኦህዴድ ስብሰባ ወቅት ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በሁዋላ መልቀቂያ እንዳቀረቡ ታውቋል። ይሁን እንጅ አሁንም በስራቸው ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የሃብሊ ባለስልጣናት እነዚህ አመራሮች “ ክልሉን የሚበጠብጡ ናቸው” በሚል በስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ እና ከስልጣን እንዲባረሩ ሲወተውቱ ከርመዋል። ሌሎች የኦህዴድ አባላት አቶ አለማየሁና አቶ ጀማል ከተነሱ ስልጣናቸውን በመልቀቅ ተቃውሞአቸውን እንደሚያሰሙ በመናገራቸው ዋናው ኦህዴድ ከግሳጼ በስተቀር ምንም ለማድረግ ሳይችል ቀርቷል።
የዛሬው ድርጊት በክልሉ ስልጣኑን በዋነኝነት በያዙት ሃብሊዎችና በምክትል ደረጃ የሚሰሩት ኦህዴዶች መካከል የተጀመረው ሽኩቻ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እየደረሰ መምጣቱን ያሳያል። የሁለቱ ድርጅቶች ባለስልጣናት አለመስማማት ህዝቡ የመብት ጥያቄዎችን እንዲያነሳ እረድቶታል። ሰሞኑን ከጅጅጋ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በመደገፉ ሲወደስ የነበረው የአቶ ሙራድ አስተዳደር ይህንኑን ድጋፍ ተጥቅሞ እነ አቶ አለማየሁን ለመምታት የነበረው እቅድ እንደከሸፈበት ዘጋቢያችን ገልጿል።
ከሃብሊ ባለስልጣናት ጋር የጠበቀ የጋብቻ እና የጥቅም ትስስር የፈጠሩት ከስልጣን የተነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሃምዛ ሙሃመድ በሰራባቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸማቸውን በቅርብ የሚያውቁዋቸው ሰዎች ይገልጻሉ።
ድሬደዋ ውስጥ በወር 9600 ብር የሚከራይ ዘመናዊ ቪላ አላቸው። ወደ ሃረሪ ክልል ከመዛወራቸው በፊት ደግሞ ትልቅ ግቢ ያለው የቀበሌ ቤት ወስደው በ1.5 ሚሊዮን ብር ሸጠዋል። ሃረር ውስጥ የግብርና ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሲመደቡ ሃረር ላይ መሬት በመውሰድ ዘመናዊ ቤት ሰሩ። ለወላጆቻቸውም እንዲሁ ተመሳሳይ ዘመናዊ ህንጻ ገንብተውላቸዋል። በአዳማ ከተማም እንዲሁ በእርሳቸው፣ በባለቤታቸውና በአማቻቸው 7 ቦታዎችን ይዘው ግንባታ እያካሄዱ ነው። ከ2007 ጀምሮ የሃረሪ ክልል ምክትል ፕራዝዳንት ሆኖ ሲመደብ ፣ የክልሉ መንግስት በወር እስከ 25 ሺ ብር የሚከፈልበት ቤት ተከራይቶላቸዋል። ለእቃ መግዣ በሚልም 2.5 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም አንድ ቨ-8 ፕራዶ መኪና ለባለቤታቸው ደግሞ ኮብራ መኪና ተገዝቶ ተበርክቶላቸዋል። የብሄር ብሄረሰቦችን በአል ምክንያት በማድረግ በሃረር በ1.8 ቢሊዮን ብር የተጀመረውና ግንባታው እስካሁን ያልተጠናቀቀውን ስታዲየምን ያለ ጨረታ ከህወሃት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው አፍሮጽዮን ኩባንያ እንዲወስደው ሲደረግ፣ እርሳቸውና የቅርብ ጓደኛቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙራድ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መቀበላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment