Monday, September 18, 2017

ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የተፈናቀለበትን ግጭት ለመፍታት ሁለቱ ክልሎች በድጋሜ ቢስማሙም አሁንም ግን ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው

(ኢሳት ዜና መስከረም 08 ቀን 2010 ዓም)ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የተፈናቀለበትን ግጭት ለመፍታት ሁለቱ ክልሎች በድጋሜ ቢስማሙም አሁንም ግን ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው
በ2009 ዓም በኦሮምያ ብቻ ከ400 ሺ በላይ ፣ በሶማሊ ክልልም እንዲሁ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉበትን ችግር ለመፍታት የኦሮምያ ክልል መሪ አቶ ለማ መገርሳና የሶማሊው ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። ሁለቱም መሪዎች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ካወጁ በሁዋላ፣ ዛሬም በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች የጭነት መኪኖችን እየተከራዩ ሃረር ከተማ መግባታቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል። 
የሶማሊው ክልል መሪ ግጭቱን ለመፍታት መስማማታቸውን ከአቶ ለማ ጋር በመሆን በገለጹበት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰሞኑን በተደጋጋሚ እርሳቸውም ሆኑ ቃል አቀባያቸው ሲናገሩት እንደነበረው፣ በአወዳይ ለተከሰተው ግድያም ሆነ በአጠቃላይ ለተፈጠረው ችግር የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናትን ተጠያቂ አድርገዋል። የኦሮምያው መሪ አቶ ለማም እንዲሁ ግጭቱ የህዝብ ለህዝብ ሳይሆን በመሪዎች የመጣ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን እንደ ሶማሊ ክልል አቻቸው ለግጭቱ በቀጥታ የሶማሊ ክልል መሪን ተጠያቂ አላደረጉም።

አቶ አብዲ ለዚህ ሁሉ ግጭትና ግድያ ዋና መሪ ተዋናይ የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ስልጣን እንዲለቁ፣ ግጭቱን ማስቆም ያልቻሉት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝም እንዲሁ ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈው ነበር። አቶ አብዲ ከአገሪቱ ባለስልጣናት የትግራይ ባለስልጣናት ብቻ ከጎናቸው እንደቆሙ ከኢትዮጵያ ህዝብም የትግራይ ህዝብ ብቻ ድጋፍ እንደሰጣቸውና ከጎናቸው እንደቆመ በእንግሊዝኛ በጻፉት ጽሁፍ ላይ ገልጸዋል። ይህን ጽሁፍ ግጭቱን ለማቆም ተስማምተናል ካሉ በሁዋላ ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አንስተውታል።
በኦሮምያ ባለስልጣናት በኩል ወቅታዊ መረጃዎችን ከፓርቲያቸው ፖሊሲ አንጻር እየተከታተሉ የሚሰጡት የኦሮምያ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው በ2009 ዓም ብቻ በአምስት ዞኖች በተካሄደው ግጭት 416 ሺ 807 ሰዎች እንደተፈናቀሉ ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት በደረሰው መፈናቀል ብቻ 55 ሺ ሰዎች ከሶማሊ ክልል ተባረው ወደ ኦሮምያ ክልል መግባታቸውን ባለስልጣኑ ገልጸዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው በአቶ አብዲ ሙሃመድ የሚመራው የሶማሊ ልዩ ሃይል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምንም እንኳ ሁለቱም መሪዎች ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ ግጭቱን ለመፍታት ተስማማን ቢሉም፣ ተፈናቃዮች ወደ ተፈናቀሉበት የሶማሊ ክልል ይመለሱ አይመለሱ፣ የወደመና የተዘረፈው ንብረታቸው ይመለስላቸው አይመለስላቸው እንዲሁም ህይወታቸውን በገፍ እንዲያጡ ያደረጉት ከፍተኛ እና ዝቀተኛ አመራሮች በህግ ይጠየቁ አይጠቁ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ግልጽ መልስ አልሰጡም። አሁንም በሶማሊ ክልል በኩል የሚፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ለማስቆም በቂ ጥረት አለመደረጉ ስምምነቱን የለበጣ አድርጎታል። የአካባቢው ህዝብ እና አባገዳዎች ሰሞኑን ተደርገው በነበሩ ስብሰባዎች ላይ አቶ አብዲ የሚባለው በደም እጁ የተጨማለቀ ሰው ከስልጣን ካልተነሳ እንዲሁም ልዩ ሃይል የሚባለው ገዳይ ሚሊሺያ ካልተበተነ ሰላም አይወርድም በማለት ተናግረዋል። በፌደራል መንግስቱ የሚመራው የመከላከያ ሃይል መፈናቀል እንዳይኖር ማስቆም ሲገባው የተፈናቀሉትን ሰዎች በማመላለስ ስራ ላይ መጠመዱን በማየት ፣ ብዙዎች የፌደራል መንግስቱን የሚያሽከረክሩት የህወሃት ባለስልጣናት ከአቶ አብዲ ጎን ቆመው ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። አቶ አብዲም በግልጽ የህወሃት ባለስልጣናት ከጎኑ መቆማቸውን መናገራቸው ህዝቡ ከእንግዲህም ሰላም ይፈጠራል ብሎ እንዳያስብ እንዳደረገው በቅርብ ጉዳዩን የሚከታተለው ዘጋቢያችን ገልጿል።
በርካታ ተፈናቃዮች በሃረር ፣ ጭናክሰን፣ ሚኤሶ እና ባቢሌ ከተሞች በድንኳን ተጠልለዉ የሚገኙትን ተፈናቃዮች ኢትዮጵያውያን ብሄር ሳይለዩ እርዳታዎችን እያሰባሰቡ የአቅማቸውን እየለገሱ መሆኑንም አክሎ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment