Wednesday, September 20, 2017

አርበኞች ግንቦት7 በበለሳ ጫካ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ነው ሲል አቃቢ ህግ አስታወቀ

(ኢሳት ዜና መስከረም 10 ቀን 2010 ዓም) አርበኞች ግንቦት7 በበለሳ ጫካ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ነው ሲል አቃቢ ህግ አስታወቀ
በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች ይፋዊ እውቅና ባይሰጥም፣ የተቃዋሚ አባላት ናቸው እየተባሉ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ግለሰቦችን በሚገልጽበት ጊዜ የተቃዋሚ ሃይሎች በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ለመሆኑ ማረጋገጫ እየሰጠ ነው።
ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር ደምቢያ ወረዳ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የተለያዩ ጥቃቶችን ፈጽመዋል በሚል ፍርድ ቤት የቀረቡ 14 ዜጎች፣ ከኤርትራ በመጡ የአርበኞች ግንቦት7 አባላት ስልጠና እንደተሰጣቸውና የተለያዩ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ እንደነበር ገልጿል። የአርበኞች ግንቦት7 አባላት በበለሳና በአርማጭሆ ወረዳዎች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገለጸው አቃቢ ህግ፣ እነዚህ ሃይሎች ለተከሳሾች ስልጠና መስጠታቸውን አትቷል።
በአማራ ክልል ምንም አይነት የአርበኞች ግንቦት7 ህዋስም ሆነ የማሰልጠኛ ቦታ የለም በሚል ተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ የነበረው አገዛዙ፣ በለሳ አርማጭ እንዲሁም ጯሂት አካባቢ የሚገኙ ጫካዎች ለወታደራዊ ስልጠና መዋላቸውን አቃቢ ህግ ገልጿል። አንድ ነጋዴና 13 አርሶአደሮች በ ደምቢያ ወረዳ ፣ መንድባ ጫካ ውስጥ ወታደራዊ ቤዝ መስርተው ከኤርትራ በመጡ አሰልጣኞች ወታደራዊ ትምህርት ወስደው በቻይና ኮንትራክተሮች በሚገነባው የሰራባ የመስኖ ፕሮጀክት ላይ ጠቃት ፈጽመው 2 ሰዎችን መግደላቸውን ገልጿል። 


እነዚሁ ተከሳሾች በበለሳና በአርማጭሆ ወረዳ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የቡድኑ አባላት ጋር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሰቃሱ እንደነበር አቃቢ ህግ በክሱ ላይ አስፍሯል።
ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የድርጅቱ የአመራር አባል እንዳሉት ጥቃት የተፈጸመባቸው ህዝብ በሚገለገልባቸው መሰረተ ልማቶች ላይ ሳይሆን፣ የህወሃት ንብረት በሆኑትና ኢፈርት ገንዘብ በሚዘርፍባቸው ተቋማትና ለዳሻን ቢራ መጥመቂያ በሚል የሚሰሩ ግድቦች ላይ ነው። የወያኔ ካድሬዎችና አመራሮችም የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርበኞች ግንቦት7 በ8 የመምሪያ እዦች በሰሜን ጎንደር ዞን አየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ ከ5 የማይበልጡ አባሎቹ በሽምግልና ስም ተታለው እጃቸውን ከሰጡ በሁዋላ ፣ “ወያኔ ቃሉን አጥፎ ወደ እስር ቤት” እንደወሰዳቸው የአመራር አባሉ ኢሳት ላቀረበላቸው ጥያቄ በጽሁፍ መልስ ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment