Tuesday, September 19, 2017

ከሶማሊ አሁንም የ ኦሮሞ ተወላጆች እየተፈናቀሉ ነው ወደ ጅጅጋ የተላኩ የህዝብ ተሽከርካሪዎች ወደ ኦሮምያ እንዲመለሱ ተደርጓል።

የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ፣ ባለስልጣኖቹ እንደፈጠሩት የተናገሩትን ግጭት ለማስቆም ቃል በገቡ በማግስቱ የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት የጥቃት ዘመቻውን አድማስ በማስፋት ከዛሬ ሊሌት ጀምሮ ከፍተኛ የቆዳ ስፋት ባላቸው በምስራቅ ጉጂ ዞን በሚገኙት ዳዋ እና ቡሌ ካሃር ቀበሌዎች ጥቃት መፈጹምን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ጥቃቱን ተከትሎ የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች የአጸፋ እርምጃ የወሰዱ ሲሆን፣ ግጭቱ ወዲያውኑ ቆሟል።

በዳዊ ቃቻ ወረዳ ኦዴ አራጋ ቀበሌ ባለፈው እሁድ በህዝቡና በልዩ ሃይሉ መካከል በነበረው ግጭት ከህዝቡ 16 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከልዩ ሃይሉ በኩል ደግሞ ከ10 ያላነሱ ወታደሮች ተገድለዋል። ዛሬ ጠዋት በተጀመረው ግጭት ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ ለማወቅ አልተቻለም።
በሌላ በኩል አሁንም የሚፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውን የምስራቅ ሃረርጌ ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ትናንት ከሶማሊ ክልል ተፈናቅለው ወደ ሃረር በመጓዝ ላይ የነበሩ ተፈናቃዮች፣ የተሳፈሩበት ሲኖ ትራክ ኮምቦልቻ ፋጤ በሚባለው ዳገት አካባቢ በመገልበጡ 6 ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ 3ቱ ሆስፒታል ገብተዋል። ( )
የሰላም ስምምነቱን በመንተራስ ከሃረር ወደ ጅጅጋ የተጓዙ “ኦሮ” የሚል ታርጋ ያላቸው የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች፣ ጅጅጋ ለመግባት 15 ኪሜ ሲቀራቸው ካራ ማራ ላይ ህዝቡን አራግፈው እንዲመለሱ ተደርጓል። ከሶማሊ ክልል የተሰጠ መታወቂያ ካልሆነ በስተቀር የሌሎች ብሄሮችን ማንነት የያዙ ሰዎች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ተደርጓል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ኤምባሲ በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በሐረርጌ የጎሳ ግጭትን እና የበርካታ ሰዎችን መፈናቀል አስመልክቶ በሚወጡ አሳሳቢ ዘገባዎች መረበሹን ገልጿል።
“ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ግልጽ በሆነ አካሄድ እንዲያጣራ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ የጠየቀው የአሜሪካ መንግስት፣ “ኢትዮጵያ ጠንካራ፤ የበለጸገች እና ዴሞክራሲያዊት ሀገር መሆን የምትችለው፤ ግልጽና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት፤ ግልጽ የመንግሥት አሰራር፤ እንዲሁም የዴሞክራሲ እና የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር ስትችል እንደሆነ” ገልጿል፡፡ የሰሞኑ ሁነቶች በተጠቀሱ ዘርፎች ይበልጥ ፈጣን እና ተጨባጭ ለውጥ አስፈላጊ እንደሆነ አመላካች ነው ሲል
መግለጫውን ደምድሟል፡፡

No comments:

Post a Comment