Monday, September 18, 2017

(ኢሳት ዜና መስከረም 08 ቀን 2010 ዓም)የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የአማራ ክልልን ክፉኛ እየተፈታተነው ቢሆንም አመራሩ ትኩረት ሰጦ እየሰራ አለመሆኑ ተነገረ፡፡
በፌደራል የሰቆጣ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ሲኒየር ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሲሳይ ሲናሞ ሰሞኑን ባቀረቡት ጥናት እንደገለፁት በአማራ ክልል አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ካሉት ህፃናት ውሰጥ 46 ነጥብ 5 በመቶ በመቀንጨር የተጠቁ ናቸው፡፡ 
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ከሁለት ህፃናት አንዱ ቀንጭሯል ፡፡ ዶ/ር ሲናም እንደሚሉት እነዚህ ህፃናት ታዳጊዎች ናቸው፡፡ ነገ ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን የሚረከቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች በመቀንጨር ተጐዱ ማለት በቀጣይ ሕይወታቸው የትምህርት ውጤታቸው ደካማ ይሆናል፤ በስራ መስክም የሚያስመዘግቡት ውጤት፣ ተፈጥሯዊ ችሎታቸውና የማምረት ክህሎታቸው ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ክልሉ ከሚያገኘው ሠራተኛ ማህበረሰብ ግማሽ ያህሉ በዚህ ሂደት ውሰጥ የሚያልፍ ይሆናል፡፡ ይህም ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ትልቅ አደጋ ነው፡፡በተለይ ጉዳቱ በሰቆጣ ተፋሰስ ባሉ 23 ወረዳዎች ላይ የከፋ ነወ፡፡ “በዚህ አካባቢ እድሜያቸው አምስት አመት ውሰጥ ከሚገኙ ህፃናት መካከል ከ60 በመቶ በለይ የሚሆኑት
በመቀንጨር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ማለት ከ10 ህፃናት መካከል ስድስቱ ቀንጭረዋል፡፡በመሆኑም በቀጣይ ዓመታት በአካባቢው የማህበራዊ፣ ኢኮኖማያዊና ሌሎች ጉዳቶች ሊመጡ እንደሚችሉ በቀላሉ መገመት ይቻላል” ሲሉ በአካባብው ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ዶ/ር ሲሳይ ያስረዳሉ፡፡
የተከዜ አካባቢ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ አካባቢ በመሆኑ “በአካባቢው ላይ ምን ስራ ቢሰራ ይሻላል? ”የሚለውን የመለየት ስራ ልምድ መቀሰሙን የጠቆሙት ዶ/ር ሲናሞ አጎራባች በሆነው የትግራይ ክልል ቃላሚኖ በተባለው አካባቢ የፌደራል መንግስት ትኩረትና ክትትል በማድረግ በአጭር ጊዜ ችገሩን እንዳስወገደው ለሰቆጣ ተፋሰስም ትኩረት ይሰጠው ዘንድ አሳስበዋል፡፡ በክልልና በፌደራል ደረጃ ያሉ ክፍተኛ የሴክተር መስሪያቤት ባለሙያዎችን በመያዝም እስራኤል በመሄድ ልምድ በመውሰድ በ23ቱ የአማራ ክልል ወረዳዎች ምን መሠራት ይቻላል የሚል ቅድመ ጥናትም መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት በኢንፌክሽን የመጠቃት እድልን ያሰፋል፤ ስቃዩንም ያከፋል፡፡ ምክንያቱም ሰውነት በሽታ ተከላካይ አንቲ ኦክሲዳንቶችን ያጣልና፡፡ እስከ ሁለት አመት ድረስ የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በተለይ ባልተወለደ ህፃን ላይ ጽንሱ ዝቅተኛ የሰውነት ክብደት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ከሁለት ሺህ 500 ግራም በታች ይሆናል፡፡ እናትየው ቀደም ሲል በአኒሚያ፣ በወባና በኤች አይቪ/ኤድስ በሽታ የተያዘች ከሆነ ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካለባትም የሚወለደው ህፃን የአእምሮ ጉዳት ሊደረስበት ይችላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በዚህ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚሰቃዩ ሰዎች ትኩረት ለማድረግ ይሳናቸዋል፡፡ በሽታ የመከላከል አቅማቸውም ይዳከማል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በምግብ እጥረት የተጐዱ ህፃናት በእድሜያቸው ልክ የሰውነት ክብደትና ቁመት አይኖራቸውም፡፡ እናም ለመቀንጨር ይዳረጋሉ፡፡
ሲኒየር ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ሲሳይ ሲናሞ አክለው እንደገለፁት የሰቆጣ ዲክላሬሽን ከታወጀበት ከ2007 ጀምሮ ስራዎች ሲሰሩ ቢቆዩም በእወጃው ወቀት የነበረው 40 በመቶ ቀንጭረው የነበሩት የአካባቢው ህፃናት ቁጥር አሁን 38 በመቶ ላይ መቆሙ ጉዳዩ ትኩረት እንዳልተሰጠው ማሳያ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ አሁን ባለው ፍጥነት ብቻ የመቀንጨርን አደጋ ለመቀነስ የሚጓዝ ከሆነ ግን ጉዳቱ ሰፊ እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚያካፍሉት ማኔጀር ይህንን ለመለወጥም ሁሉም የከተማና የክልል ኃላፊዎች ጉዳዩን በባለቤትነት በመያዝ ቁርጠኝነታቸውን እንዱያሳዩ ጠይቀዋል፡፡ (ድምጽ-መቀንጨር-01)
የእለቱን ስብሰባ ሲመሩ የነበሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከፍተኛ ችግር መሆኑን አምነው በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ በመያዝ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ችግሩ ካልተፈታ የክልሉን የሰው ኃይል አመናምኖ የክልሉን ቀጣይ ትውልድ ከፍተኛ ጉዳት ላይ እንደሚጥለው ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. 2013 'ኮስት ኦፍ ሀንገር ኢን አፍሪካ' በሚል በ12 የአፍሪካ ሀገራት በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ በምግብ እጥረት 3ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ጥናቱ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ በኢጋድ፣ በተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለአፍሪካ እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም ትብብር መሠረት የተካሄደ ነበር፡፡ እናም በጥናቱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ ታውቋል፡፡ ጥናቱ እንዳስታወቀው ከአምስት ኢትዮጵያዊ ህፃናት መካከልም ሁለቱ በምግብ እጥረት የተጠቁ ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment