Thursday, September 25, 2014

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የፖለቲካ ስልጠናውን ተቀላቀሉ…

ኢሳት ዜና ፦ መንግስት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የትምህርት መመሪያን ለማጥመቅ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ በአገሪቱ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስልጠናውን በግዳጅ እንዲወስዱ እየተደረጉ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎቹ የፖለቲካ ስልጠና እንዳለ አስቀድመው በመስማታቸው፣ ከስልጠናውን የቀሩ ሲሆን፣ የገዢው ፓርቲ የወረዳ ሹሞች መምህራን ተማሪዎችን እንዲያመጡ የተለያዩ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ እያግባቡ ነው።

አንድ መምህር ለኢሳት እንደገለጹት፣ ከተማሪዎች በፊት የተደረገው የመምህራን ስልጠና ያለውጤት ከተበተነ በኋላ፣ ተማሪዎች ስለሰላም እና ስለትምህርት ስርአት ስልጠና ይወስዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ ስልጠናውን ለመውሰድ በአካል የተገኙት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ሆኖ መገኘቱንተናግረዋል። መስከረም 5 ይጀመራል የተባለው ትምህርት በፖለቲካ ስልጠናው የተነሳ እስከ አሁን አለመጀመሩን የተናገሩት መምህሩ በዚህ ሁኔታ በሚቀጥለው ሳምንት መደበኛው ትምህርት ይጀመራል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

በከፍተኛ ምሬት ውስጥ የሚገኙ መምህራን ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑም አክለው ገልጸዋል ነገረ ኢትዮጵያ ዛሬ በሳራጨው ዘገባ ተማሪዎች ‹‹ እኛ እድሜያችን ከ18 ዓመት በታች ነው አንመርጥም፣ ለምን ትጨቀጭቁናላችሁ፣ ኢህአዴግ አይመረጥም››የሚሉ አስተያየቶች በመስጠታቸው ፖሊስ «እየረበሻችሁ ነው» በሚል እያስፈራራቸው መሆኑን ገልጿል። የፌደራል ጉዳዩች እና የትምህርት ሚኒስቴር ባወጡት የጋራ ዕቅድ መሰረት ማንኛውም የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነባሩ ተማሪ ከመግባቱ በፊት ከመስከረም 16 ቀን ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቆ ተማሪዎች ጥሪ እየተደረገላቸው ነው።


No comments:

Post a Comment