Wednesday, September 3, 2014

ኢህአዴግ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ለሰራተኞች የሚሰጠውን ስልጠና ለማስቀጠል አቅዷል

 ኢሳት ዜና :-ለሁለት ሣምንታት ለዩኒቨርሲቲ አዲስና ነባር ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የመጀመሪያ ዙር
አስገዳጅ ሥልጠና የፊታችን ቅዳሜ የሚጠናቀቅ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ሥልጠና ወዲያውኑ ለመቀጠል ትምህርት ሚኒስቴር መዘጋጀቱን መረጃዎች ጠቁመዋል።
ተማሪዎች ተገድደው በገቡበት በዚሁ የሥልጠና ቆይታቸው ደስተኛ ያለመሆናቸውን በመናገር ላይ ናቸው፡፡
በዋነኛነት የመንግሥት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለተማሪዎች ለማስተዋወቅ በሚል በመንግሥት ከፍተኛ በጀት ከ33 በላይ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጠው በዚሁ ሥልጠና ላይ የኢህአዴግ ዋና ዋና ካድሬዎች በአሰልጣኝነት የግንባሩን ርዕዮተ ዓለም ለማስተዋወቅና ለማስረጽ
ሲጠቀሙበት ከርመዋል። ተማሪዎቹ በሥልጠና ቆይታቸው ከምግብና የታሸገ ውሃ መጠጥ በተጨማሪ በቀን 35 ብር ውሎ አበል የታሰበላቸው ሲሆን በአንድ ለአምስት ተጠርንፈው የቀን የውይይት አጀንዳዎችን እንደገና እርስ በእርስ ተወያይተው እንዲመጡ አስገዳጅ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑና በዚህም በሒደቱ በከፍተኛ ደረጃ መሰላቸትና የእርስ በእርስ አለመተማመን እንዲፈጠር መሆኑ እንዳሳዘናቸው በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡

ትምህርትና ሥልጠና በፍላጎትና በምርጫ የሚወሰድ መሆኑንና ላለመገደድ ያላቸውን ሕገ መንግስታዊ መብት በገዥው ፓርቲ ከመነጠቃቸውም በተጨማሪ በአስገዳጅ ሁኔታ የገዥውፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ለማስረጽ የሚደረገው ጥረት አብዛኛውን ተማሪ ይበልጥ ለግንባሩ ያለውን ጥላቻ ያሳደገነው ሲሉ ተችተውታል፡፡ በዚሁ ሥልጠና ላይ ስለሙስናና ብልሹ አሠራር መስፋፋት፣ስለፍትህ መጓደል፣ስለሰዎች አለአግባብ መታሰር፣ስለኑሮ
ውድነት ፣ስለኤሌክትሪክ፣ውሃ እና የቴሌኮም አገልግሎቶች ጥራት ማሽቆልቆል እና የመሳሰሉ ሀገራዊ የሆኑ
ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተማሪዎቹ በአስተያየትና በጥያቄ መልክ ያቀረቡ ቢሆንም ካድሬዎቹ ለእነዚህ ጥያቄዎች
ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ «ይህ የጸረ ሰላም ሃይሎች፣የኪራይ ሰብሳቢዎች አስተሳሰብ ነው…» የሚሉ ምላሾች
ሲሰጡ በመደመጣቸው ተማሪዎቹ በእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ሀገሪትዋ እየተመራች መሆንዋ ይበልጥ ሀዘኔታና ግራ መጋባት እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡ ኢሳት ከተማሪዎች ጋር ያደረገውን ውይይት በተከታታይ ቀናት እንደሚለቅ ለመግለጽ ይወዳል።
በሌላ ዜና ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢህአዴግ ጽ/ቤት ባዘጋጀው የድርጅት አባሎች ስልጠና መርሃ ግብር መሰረት ለከተማው በየደረጃው ለሚገኙ ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ የኢህአዴግ አባሎች ዛሬ በይፋ ስልጠና ጀምሯል፡፡
ስድስት ኪሎ በሚገኘው ሚኒልክ ት/ቤት የሚካሄደው ስልጠና ከዛሬ ነሃሴ 27 ጀምሮ ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናትይካሄዳል።
ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ ከ50-100 ብር አበል እንደሚከፈል ታውቋል። በስልጠናው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ዘገባዎችን ለወደፊቱ ይዘን እንቀርባለን።
ኢህአዴግ ለመስተዳድሩ የፖሊስ አባላትም ተመሳሳይ ስልጠና እያሰጠ ይገኛል።


No comments:

Post a Comment