Thursday, September 25, 2014

ለህወሃት የማስጠንቀቂያ ደወል!



ይህንን ደብዳቤ የምጽፍላችሁ ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን በተውጣጣው የማኅበራዊ ፍትሕ እንቅስቃሴ ከሚመራው በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ስም ቢሆንም በተለይ ግን ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች እንደመሆናችን እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ አባል የላኩላችሁ ደብዳቤ መሆኑን እንድታውቁልኝ እወዳለሁ። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አለመግባባት ሲከሰት ሁኔታውን ማብረድና ወደ መልካም ማምጣት የቤተሰቡ አባላትና ስለቤተሰቡ በጥልቀት የሚያስቡ ሽማግሌዎች ዋንኛ ተግባር ነው። ታዲያ እኛም አንድ አገርና አንድ ተስፋ በፊታችን ያለ እንደመሆኑ በመካከላችን ያለውን ችግርና ግጭት በእውነትና በታማኝነት ልንነጋገር ይገባል ብዬ ከማመን ነው ይህንን የምጽፍላችሁ።የዚህ ደብዳቤ ዋና ዓላማ የህወሃትን ሊቀመንበር፣ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የትግራይ ተወላጅ ወንድምና እህቶቻችንን በሙሉ፤ ስለ እያንዳንዳችን ጣት እንድንጠቋቆም ሳይሆን እርስበርሳችን መነጋገር እንችል ዘንድ ለመጋበዝ ነው። ይህም ንግግርና ውይይት ከፍ ብሎ ወደ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲያመራ ለማድረግ ነው። ከዚህ አንጻር ይህንን ደብዳቤ በምጽፍበት ጊዜ ህወሃትን ከትግራይ ሕዝብ በመለየት ለማስቀመጥ ያደረኩትን ሙከራዎች በሙሉ ልብ እንድትሏቸው እሻለሁ። የዚህ ደብዳቤ አግባብ በሥልጣን ላይ ላሉቱና ላጋዦቻቸው ነው እንጂ ብዙውን ጊዜ አለአግባብ ከህወሃት ጋር አብረው የሚወቀጡት የትግራይ ወገኖችን ደርቤ እየተናገርኩ አለመሆኑን እንድታስተውሉልኝ ይሁን።ይህንን ደብዳቤ የምጽፍላችሁ በጥላቻ በመነሳሳት ሳይሆን በፍቅርና መልካምን ሁሉ በማሰብ እንደሆነ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም የህወሃት ዘረኛ ፖሊሲ ከህዝቡ ጋር ተቆራኝቶ በአገራችን በቂ ምሬትና ጥላቻ በትግራይ ወንድሞችና እህቶቻችን ላይ እንዲኖር በማድረጉ እኔ በዚያ ላይ ሌላ ጥላቻ የመጨመር ምንም ፍላጎት የለኝም። እንዲያውም ከአምስት ዓመት በፊት የአደባባይ ምስጢር የሆነውን እውነታ በማፍረጥረጥ በህወሃት እየተገበረ ያለው የዘር መድሎና አፓርታይድ ሥርዓት እያደረሰ ያለውን በግልጽ አስረድቼ ነበር። የዚያን ጊዜ የጻፍኩት ደብዳቤ እዚህ ላይ ይገኛል። (http://
www.solidaritymovement.org/090611OpenLetterToMyFellowTigrayans.phpይህ የአሁኑ ደብዳቤ ከዚያ የቀጠለ ሲሆን የዚያን ጊዜ እንዳልኩት ጉዳዩን እያቀረብኩት ያለሁት እንደ አንድ ባለሙያ ሳይሆን እንደ አንድ ተራ ሰው ለማኅበረሰቤ መልካም በማሰብ ማበርከት የሚገባኝን ከመጠቆምና ለወደፊቱ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለእናንተ ለራሳችሁ የሚጠቅም ነገር ከማሳየት አኳያ ነው።   እኔ እዚህ ደብዳቤ ላይ እውነቱን አሰፍራለሁ ብልም በተጻፈው ነገር ሁሉ ከኔ ጋር ትስማማላችሁ ብዬ አልጠብቅም፤ ነገር ግን ሁለታችንንም የሚያስማማ አንዳንድ ነጥቦችን እናገኛለን ብዬ አምናለሁ።እኛ ማነን?ኢትዮጵያ በምትባለው አገር በመወለዳችን ወይም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ያለን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ነን። ከሚታወቀው ፍጥረተ-ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ በሚኖርባት በዚህች ምድር፤ ሁላችንም በውቅያኖስ፣ በአህጉር፣ በተራራ፣ በአገራትና ሰው ሰራሽ በሆኑ ድንበሮች ተከልለን እንገኛለን። በዚህ ውስጥ ሁሉ በልዩነታችን የምንከፋፈል ሰዎችም ነን።በኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸው ቋንቋ፣ ባሕልና ልዩ አኗኗር ያላቸው ከ80 በላይ የጎሣ ቡድኖች ይገኛሉ። በእርግጥ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት እነዚህን ቡድኖች “ብሔር ብሔረሰቦች” ተብለው ይጠራሉ። የዚህ ዓይነቱ የመንግሥት አስተዳደር በተለያዩ ቡድኖች መካከል እኩልነት እንዲኖር ማድረግ ሲገባው እውነታው ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተገፋና የተተወ መሆኑን ነው የሚያሳየው። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ጤናማ መተሳሰብና መረዳዳት በኢትዮጵያችን ውስጥ በሚገኙ “የብሔር ቤተሰቦች” ሲከሰት አይታይም። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች ከዚህ “የብርቅየ ልጅነት” ጎራ ለመመደብ በመፈለግ ደፋ ቀና ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ እንደ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ባለመቆጠራቸው ምክንያት አሁን አለ የሚባለውን ግንኙነት “መቁረጥ” ይፈልጋሉ። የእነዚህኛዎቹ አቋም ጠንከር ያለ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶቹ እናንተ ህወሃቶችን ሥልጣን እንድትለቁ የሚጠይቁ ሲሆኑ ከዚያ ጋር አብሮ ለራሳችሁ ያጋበሳችሁትን ልዩ መብትና ጥቅማጥቅም አብራችሁ እንድትሰጡ ይጠብቁባችኋል። እንደዚህ ወገናዊ እና ሁሉንም እኩል በማይመለከት ቤት ውስጥ እንዴት ነው ሌሎች ኢትዮጵያውያን መኖር የሚችሉት? እንዴትስ ነው በእንደዚህች ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚመኙት? እስካሁን እየታየ ያለው ተቃውሞ እና ንቅናቄ እናንተ ህወሃቶች በአንድም ይሁን በሌላ ሁኔታ መላ እንድትፈልጉ እያስገደዳችሁ ያለ ሁኔታ ነው።  ይህንን መንገድ የምትከተሉት ግን በዕርቅና ተሃድሶ ስም ከዚህ በፊት እንዳደረጋችሁት በሥልጣናችሁ ለመቆየት የምታደርጉት ብልጣብልጥ አካሄድ ሳይሆን መደረግ ያለበት አስፈላጊና እውነተኛ ነገር በመሆኑ ልትፈጽሙት የሚገባ ስለሆነ ነው።ፈጣሪ የሰጠውን ዓለምአቀፋዊ ሕግ መከተል ሰላምን ያወርዳል!ፈጣሪ ኃያሉ አምላክ ለማንም አያዳላም፤ እኛንም እንዲሁ እንድንሆን ይመክረናል። ፍትሕን ለታናናሾችም ሆነ ለታላላቆች እንዲሁም ከእኛ ጋር ላሉትም ሆነ ከእኛ ውጭ ለሆኑት እንድናሰፍን ይጠበቅብናል። ሌሎችን ስንንቅ፣ ከሰው በታች ስናደርግ፣ ስናገልል፣ ስናጣጥል፣ ስንበድል ወይም ስናጎሳቁል ይህንን ሁሉ ቆጥሮ በእኛ ላይ ተመልሶ መምጣቱ የማይቀር ሐቅ ነው። እኛ እንደ ኢትዮጵያዊ የሌሎችን መብት ስንጠብቅ፣ ማንነታቸውን ስናከብር ፈጣሪ የለገሳቸውን መብት ሁሉ በግልም ሆነ በጋራ ስናከብር የሥራችንን መልካም ውጤት እናገኛለን። ይህንን ሳንፈጽም ከቀረን ግን የዘራነውን ማጨዳችን የማይቀር ነው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሁሉም በራሱ ንዑስ ማንነት ላይ በማተኮር በሌሎች ላይ የሚደረገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ትክክለኛነት ለማስረዳት ሲጠቀምበት ይስተዋላል።  አኢጋን የተቋቋመውም ይህንን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየርና “ሌሎች” እያልን የምንጠራቸውን የራሳችን አድርገን እንድንወስድና ከፈጣሪ ጋር ስምምነት እንዲኖር ለማድረግ ነው። እንደው እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኃያሉ ፈጣሪ አንድ ሰው እንደ “እኛ ካልተናገረ” ወይም “እኛን ካልመሰለ” ወይም “የእኛን ዓይነት” ሃይማኖት ከሌለው ወይም “ከእኛ ጎሣ/ብሔር” ውጭ ከሆነ ወዘተ ለይቶ የሚያየው ይመስለናል? ወይም ይህ ሰው “የእኛን ዓይነት” የፖለቲካ አመለካከት ከሌለው ወይም በጣም ዝቅተኛና የተዋረዱ ከሚባሉ ጎሣዎች የመጣ በመሆኑ አምላክ ከእኛ አሳንሶ ይመለከተዋል ብለን እናስባለን እንዴ? ልናስታውስ የሚገባን ነገር ቢኖር ከአካል ሰውነታችን አንዲቷም ክፍል ብትሆን ከታመመች ሌላው የአካል ክፍላችን በጠና ይታመማል፤ ሰላም አይኖረውም። ታዲያ ህወሃት በኢትዮጵያችን ውስጥ ያሰራጨው የዘርና የጎሣ ፖለቲካ ያመረቀዘው ቁስል ህመም እናንተንስ ተሰምቷችሁ ያውቅ ይሆን?በዘር ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ አወቃቀር የጎጠኝነት፣ የፊውዳላዊነትና የማርክሲስታዊነት ጣምራ ውጤት ነው። – አንድን ጎሣ ወይም ጎጥ (የትግሬን) ከፍ በማድረግ በአፓርታይዳዊ አሠራር “አንዱ ጎሣ/ጎጥ ሁሉንም ነገር ለራሱ ማድረግ አለበት” ወይም ። – አንድን ቡድን ወይም ጎሣ ወይም ወገን ከሌላው የተለየ፣ የተሻለ፣ የተመረጠ፣ የበቃ፣ ስለሆነ የመግዛት/የመምራት መብት አለው፤  ስለሆነ ትርፉንም ለራሱ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፤ ሌሎች ዕድለቢሶች በሥሩ የመሆን ግዴታ አለባቸው የሚል ነው። – የሚቃወሙትን ሁሉ – ትግሬዎችንም ጭምር – የመርገጥ ባህርይ ሲሆን ከፊውዳላዊነት በተለየ መልኩ ህወሃት በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ “ሰፊውን ሕዝብ” እየጠቀምኩ ነው ቢልም በተግባር ግን  ይህ ዓይነቱ አታላይ ስልት ብዙሃኑን የአገራችንን ሕዝብ ከሌላው እንዲከፋፈል ያደረገ ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑ ያልተማረ፣ በድህነት ላይ የሚገኝና ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚለውን በልዩ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገ ነው። ይህ ዓይነቱ መርህ ተግባራዊ በመሆኑ ስንቱ የአገራችን ሕዝብ ተከፋፍሎ ቀረ? ስንቱስ “እርስ በርሱ በጠላትነት” እየተያየ ያለፈውንና አዲስ ግጭቶችን እያጎላ “ሰፊውን ሕዝብ” ለራሱ መጠቀሚያነት ያዋለው ስንቱ ነው? ህወሃት ይህንን መሠሪ ስልት በመጠቀም ተዋደውና ተከባብረው የኖሩትን፣ ለምሳሌ አማራና ኦሮሞዎችን፣ እርስበርስ በማጋጨት ክፉ ተግባር ላይ አውሎታል። ይህ ከሆነ ዘንዳ ታዲያ በግማሽ ኦሮሞ እና በግማሽ አማራ የሆኑ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ዓይነት ጥምረት ውልድ የሆኑ የት ይድረሱ? የእንደነዚህ ዓይነት ኢትዮጵያውያን እርስበርስ ግጭትና አለመግባባት በእናንተ ህወሃቶች እየዳበረና እየተደጎመ ቆይቶ እዚህ ደርሰናል። በዋንኛነትና በዓላማ ስታራምዱት የቆያችሁበት ስለሆነ እያንዳንዷ መረጃ ከእናንተ የተሰወረች ልትሆን አትችልም።ይህ ብቻ አይደለም፤ እናንተ ህወሃቶች ለአገሪቷ እጅግ የሚጠቅሙ የተማሩ ሰዎችን አሁን እናንተ ለምታራምዱት ፖሊሲ ተቃዋሚ በመሆናቸው ብቻ አስወግዳችኋል፤ እስካሁንም ጥቃት እያደረሳችሁባቸው ይገኛል። እነዚህ በምሁራን ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ የእናንተ ጥቃት የደረሰባቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ጉዳይ፣ ተቀባይነት ያላቸውን ግለሰቦች፤ እንዲሁም ከእናንተ ውሸትና በሃሰት ለፈጠራችኋትና የጥቂቶች ብቻ ላደረጋችኋት ኢትዮጵያ አልገዛም የሚል ሁሉ በሁሉም ብሔር የሚገኝ የእናንተ የጥቃት ሰላባ ሆኗል።  ዓይን ያወጣው ውሸት እንዳለ ሆኖ በማርክሲስታዊ ርዕዮት መልክ የሚቀርበው “የአገም ጠቀም” እና መልካም የሚመስለውን ብቻ ለይቶ በማቅረብ ሕዝቡ እንዲወናበድ የሚደረገው አካሄድ በአጸያፊነቱና በአሳፋሪነቱ የሚጠቀስ ነው። ይህንን በማድረጋችሁ ሕዝብን ሳያውቅ በጭፍን ለመምራት ያስቻላችሁ ቢመስላችሁም  ህወሃት የተለየ ሊሆን ይችል ነበር! ዕድሎች ነበሯችሁ ግን አልተጠቀማችሁበትም!ህወሃት በተመሠረተበት ወቅት እንደ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ትግሬዎች በደርግ አገዛዝ በደል ደርሶባቸዋል፣ ተገልለዋል፣ … የሚል እንደነበረና ይህም በረሃ እንዳስገባችሁ ራሳችሁ የምትመሰክሩት ነው። ሆኖም የሥልጣን መንበሩን በተቆጣጠራችሁበት ጊዜ ለውጥ የማምጣት ምርጫ ነበራችሁ። በሥልጣን በቆየ መጠንም ከደርግ እጅግ እያስከፋና እያስመረረ መጥቷል። ነጻ አውጪ ግምባራችሁ “ለውጥ አመጣለሁ” በማለት ሥልጣን የተረከበ ቢሆንም በጨበጠውን ሥልጣን በመጠቀም የራሱን ጦር ሠራዊት መሥርቷል፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት ንብረት በራሳችሁ ስምና በህወሃት ቁጥጥር ሥር አደረጋችሁ፤ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች በጋምቤላ፣ በኦጋዴን፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በአማራ እና በአዲስ አበባ ሕዝቡ ተቃውሞውን ሲያሰማ በእናንተ ቁጥጥር ሥር ያለው የጦር ሠራዊትና ፖሊስ ተቃውሞ የሚያሰሙትን ወይ ያስወግዳቸዋል ወይም በግድ ዝም እንዲሉ ያደርጋል። ይህ የሚፈጸመው ደግሞ በመግደል፣ በማሰር፣ የሰብዓዊ መብት በመርገጥ፣ ሕዝብን በማሸበር፣ ወደ ሌላ አገር እንዲሰደድ በማድረግ፣ ወዘተ ሲሆን አገር ቤት የሚቀረው ደግሞ በግድ ጸጥ ይደረጋል፤ ወጥታችሁ መግለጫ ስትሰጡም ሆነ ስለ ልማት ስታወሩ ይህ ሁሉ ግፍ በአገራችን ላይ እንዳልተፈጸመ ስታስመስሉ ሁለት ዓስርተ ዓመታትን አሳልፋችኋል። አገራችንን ላለፉት 23ዓመታት ስታልቧት ከቆያችሁ በኋላ በረሃ በነበራችሁበት ወቅት እና እስካሁን ድረስ “ነፍጠኛ አማራ” እያላችሁ ስታማርሩት የነበረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተ በደርግ ላይ ከነበራችሁ መራርነት ባለፈ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ነው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መመሥረት አንዱ ምክንያት። እናንተ እስካሁን ስታደርጉት የቆያችሁት ፍጹም የተሳሳተና መሰሪ ነው።  ላለፉት ዓመታት ሕዝቡን አንድ የማድረግና ለውጥ የማምጣት ዕድል ነበራችሁ። ከዚህ ይልቅ ግን በአገሪቷና በሕዝቡ ላይ መከፋፈልን እንዲሁም መተላለቅን የሚፈቅድ ወራዳ ሥርዓት ነው የፈጠራችሁት። ታዲያ በራሳችሁ ያመጣችሁትን ይህንን ሁሉ ችግር እንዴት ነው ልትጋፈጡት የምትችሉት? “ብሔር ብሔረሰቦች” በሚል ቅዠት ኢትዮጵያን መሠረትን አላችሁ። ይህ ትክክል እንዳልሆነ በማስረዳት እውነቱን የተናገሩትን ሁሉ በመግደል፣ በማሰር፣ በማስወገድ፣ ደብዛቸውን በማጥፋት፣ ወዘተ ህወሃት ከእውነት ጋር በሚጋፈጥበት ጊዜ የሚያሳየውን አሳፋሪ ገጽታ ቁልጭ አድጋችሁ በገሃድ አሳያችሁ።  ከእናንተ መካከል አንዳንዶች አሁንም እልኸኛና እብሪተኛ በመሆን ልባቸውን አደንድነው ሊሆን ይችላል፤ ህወሃት የሚዲያውን መስክ ለራሱ ጥቅም እንደተቆጣጠረው የተመሰከረ ቢሆንም በተለይ ሰሞኑን የወጣ መረጃ እንዳመለከተው በየድረገጹ ለሚወጡ ጦማሮች እና አስተያየቶች እናንተ በገንዘብ የገዛችኋቸው ቅጥረኞች ማንነታቸውን በመደበቅ ምላሽ እየሰጡ የህወሃትን መልካምነት እንደሚሰብኩና የአጸፋ ፕሮፓጋንዳ እንደሚነዙ የተደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።  ለተሻለ ወደፊት አማራጩ እውነተኛ ለውጥ ብቻ ነው! የይስሙላ ተሃድሶ ተቀባይነት የለውም!ሁኔታዎች አሁን ባሉበት ዓይነት እንደማይቀጥሉ እሙን ነው፤ መጨረሻው ይመጣል።  ሆኖም ማናችንም ብንሆን ይህ ሲከሰት ማየት አንፈልግም። ስለዚህ የዚህ ደብዳቤ ዋንኛ ዓላማም እናንተ ይህንን እንድትረዱ ለማድረግና ሁኔታው እንዳይከሰት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ለማሳወቅ ነው።እናንተ አሁን ድረስ የምትከተሉት ፖሊሲዎች ሁሉ ሲወጡና ሲቀምሙ የኖሩት በቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ነበር።    በአንድ አገር ላይ አንድ ቡድን ለብቻው ሁሉንም ነገር ሲቆጣጠር የሚከሰተውን ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም – ሩዋንዳ ቅርባችን ናት። በመጋቢት ወር 1988ዓም በሩዋንዳ የሆነው አሳዛኝና ሰቅጣጭ ድርጊት የተጀመረው በዚያው በመጋቢት ወር አይደለም። ይልቁንም ለዓመታት የወሰደ አፓርታይዳዊ የዘር ፖሊሲ አንዱን ዘር የበላይ በማድረግ፣ ሥልጣን ለራስ ወገን ብቻ በማድረግ፣ ኃብትን ለራስ ወገን በማግበስበስ፣ ሌሎችን በማሰር፣ በመግደል፣ በማሰቃየት፣ … ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር። አሁን ግን ከ20 ዓመታት በኋላ ሩዋንዳውያን እስካሁን ቁስላቸውን ለማሻር አልቻሉም፤ ለውጦች ቢኖሩም የቁስሉ ጥልቀት እና የፈሰሰው ደም ያረጠበው መሬትና የሞላው ወንዝ አለመተማመንን ቢያሰፍንም ዕርቅን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ በፈውስ ሂደት ውስጥ ይገኛሉ። ብዙዎች በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ቀጣይ ሩዋንዳ ልትሆን ትችላለች እያሉ ነው። በ1997 ምርጫ መለስና የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የቅንጅት አመራሮችን በትግሬዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል ብላችሁ የፈጠራ ክስ መስርታችሁ ነበር።  በወቅቱ በሥልጣን ለመቆየት ስትሉ እና ተቃዋሚዎቻችሁን ለማክሸፍ ብትጠቀሙበትም ተክላችሁ የሄዳችሁት ግን በአገራችን የዘር እልቂት እንዲነሳ የሚያደርግ ፈንጂ እንደሆነ ራሳችሁ ምስክርና ተጠያቂ ናችሁ።   ሁኔታው ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ለአገሪቷም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው በማሰብ አንድ መላ መፈለግ እንዳለበት ይወተውታሉ።“ልማት፣ ህዳሴ፣ …” እያላችሁ እውነታውን ለመደበቅ ብትሞክሩም ውጥረት ከነገሠ ግን ቆይቷል።  በኤርፖርቱ ውስጥ ያሉት የጉምሩክ ሠራተኞች ትግሬዎች መሆናቸው አንዱ ማረጋገጫ ነው። (በነገራችን ላይ ይህ በራሱ ወደ አገር ውስጥ ማን እንደሚገባ ማን ከአገር እንደሚወጣ በታማኞች ለመቆጣጠር ሆን ተብሎ የተደረገ ነው።)ከበርካታ ክስተቶች መካከል አንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ልጥቀስ፤ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የያዘ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ በቦሌ በሚገባበት ወቅት የጉምሩክ ሠራተኛው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ቀረጥ ይጭንበታል (በብዙ ሺዎች የሚቆጠር)። ግለሰቡም ይህንን ያህል ለመክፈል እንደማይችል ይናገራል። ይህን ጊዜ የጉምሩክ ሠራተኛው ዕቃው እንደሚወረስ (ወደ ጉምሩክ እንደሚገባ) ይነግረዋል።  የጉምሩክ ሠራተኛውም በመደነቅ ለግለሰቡ በሰጠው ምላሽ   ሲሰናበትም ሱፐርቫይዘሩ ግለሰቡን እንዲህ ይለዋል፤  በማለት አሰናብቶታል። እውነቱ ግን ግለሰቡ ትግሬ ሳይሆን አብሮ በማደጉ ቋንቋውን አቀላጥፎ የሚናገር ነበር። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱና ከዚህም ያለፈ የረቀቀ ስንት ኢፍትሃዊነት ይፈጸም ይሆን?  በአሁኑ ወቅት ባለው ሁኔታ ለበርካታ መቶሺዎች ለሚሆኑት ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች ዕርዳታ ለማደረግ የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። ይህንን ወርቃማ ዕድል አታባክኑት!ባለፉት 60ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ በአምባገነናዊ ሥርዓት ሥር ስትገዛ ኖራለች። ከዚህ አንጻር ሕዝባችን በቂ ግፍ፣ መከራ፣ ስቃይ፣ ደም መፍሰስ፣ ሰቆቃ፣ … አልተቀበለም ትላላችሁ? የብዙዎች ቤት ፈርሷል፣ የበርካታዎች ንጹህ ደም ፈሷል፣ የብዙዎች ልብ ደግሞ በቂም፣ በበቀል፣ በጥላቻ፣ በምሬት ተወጥሯል።  ማን እንደነበርን እና አምላክ የሰጠንን ሰብዓዊነት ለጥቂት ጊዜ እናጢን። የሰዎች ስግብግብነት በመንግሥታት ሕግ ውስጥ እየተሰነቀረ ለሕዝባችንና ለመጪው ትውልድ እርግማን አትርፈናል። ከራስ ወዳድነት እና ለራስ ወገን ወይም ዘር ብቻ ከማሰብና ከመሥራት ይልቅ በአገራችን በበርካታ ወገኖች ዘንድ እንደሚታወቀው ያለውን ማካፈል የተለመደና የተቀደሰ ተግባር እንደገና የምንፈጽምበት ጊዜ አሁን ነው።  በተለይ እናንተ በህወሃት/ኢህአዴግ አማካኝነት ሥልጣን ከጨበጣችሁ በኋላ የራስ ወዳድነቱና ወገናዊነቱ መጠን እየከፋ ከመሄዱ የተነሳ ባሁኑ ወቅት ሲከሰት ማየት ምንም የማይገርም ነገር ሆኗል።በአገራችን የተለመደው አብሮ የመካፈል ባህል የግራው አስተሳሰብ አቀንቃኞች እንደሚሉት ሃብትን ማሰራጨት አይደለም። የአንዱን ሃብት ወስዶ ለሌላው መስጠት በፍጹም ትክክለኛ ተግባር አይደለም፤ ሌላው ዓይነት ሌብነት ነው።   እንዲህ ዓይነቷን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር እኔም ሆንኩ ሌሎች የማይፈልጉበት ምንም ምክንያት የለም። ለመጪው ትውልድም ማውረስ የምፈልገው ይህንኑ ነው። እናንተስ? እውነትን መካድ ማንም አይችልም! ሥልጣን በወሰዳችሁበት ጊዜ አንድ ወርቃማ ዕድል አመለጣችሁ። ሌሎችን ሁሉ ማስተባበር ስትችሉ አሻፈረኝ አላችሁ።  ብዙዎችን አስመረራችሁ፤ አስከፋችሁ።    ለዚህም ነበር ለቀድሞው መሪያችሁ መለስ፣ ለትግሬዎችና ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት በላኩት ደብዳቤ ሁኔታዎችን ሁሉ ዘርዝሬ ለማስረዳት የሞከርኩት።  ይህንን ከጻፍኩ በኋላ በርካታ የተለያዩ ምላሾችን ከትግሬዎች ያገኘሁ ሲሆን በዚህ አግባብነት በሌለው የሃብት ስርጭት ዙሪያ ትግሬዎች ስለመጠቀማቸው የሰበሰብኩትን ምላሽ በዚህ መልኩ ጠቅለል አድርጌ አቅርቤዋለሁ።ይህ አስተሳሰብ እውነተኛ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ብዙዎቻችን ስለ ትግራይ ስናስብ ትግሬ የሆነ ሁሉ ደልቶታል፣ ተጠቀሟል በሚል ማጠቃለያ ሁሉንም በአንድ በመፈረጅ ስህተት እንፈጽማለን። በትግራይ የሚገኙትን ድሆች ለመርዳት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ይካሄዳሉ፤ ይህ በመሠረቱ መልካም ነገር ነው፤ እንደ ዜጋ ቢረዱ ልንደሰት ይገባናል።  ለምሳሌ እኔ ራሴ በ1993ዓም በጋምቤላ የልማት ፕሮጀክት ለማቋቋም በምንቀሳቀስበት ጊዜ ወደ ትግራይ እንድሄድና እዚያ ኢንቨስት እንዳደርግ ግፊት ተደርጎብኝ ነበር። የተሰጠኝም ምክንያት “እዚያ በርካታ መረዳት ያለባቸው አሉ” የሚል ነበር። ባላውቅ ኖሮ እታለል ነበር፤ ነገር ግን ጥያቄውን ውድቅ አደረኩት።ህወሃት ሥልጣን በመቆጣጠሩ ሁሉም ትግሬ ደልቶታል ማለት አይቻልም። ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም  በሚል ርዕስ በቅርቡ በጻፉት ጦማር እንዲህ ይላሉ፡- “የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ “ያመኛል” ማለቱ ይገባኛል።”ከዚህ አንጻር ሁሉም ተጠቃሚ እንዳልሆነና የትግራይ ሰዎች የተገለሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። ይህንን አስተሳሰብ ከሚያራምዱት መካከል አንዱ ወገን በትግራይ ልማቱ እየተካሄደ መሆኑን እና ለትግራይ ሰዎችም የተሻለ ዕድል እንደተሰጣቸው ያምንና ይህ ሁሉ መሆን ያስፈለገው ትግሬዎች ይህ ስለሚገባቸው ነው የሚል ነው።  በእርግጥ ትግሬዎች ብቻ ናቸው ደርግን ያስወገዱት? ትልቁን ድርሻ ተወጥተው ይሆናል፤ ግን ሌሎችም በዘር ተደራጅተው ሲፋለሙ እንደነበር ታሪካቸው ይመሰክራል። ከእነዚህ መካከል የኦሮሞ፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ፣ የሲዳሞ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል፣ … አርነት ንቅናቄዎች ተጠቃሽ ናቸው።     በፈጣሪ ዘንድ እናንተ አደረጋችሁትም ሌሎችም በናንተ ላይ አደረጉት የሚለወጥ ነገር የለም፤ የሁሉንም በደል የሚመለከት ነውና። ይልቅ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሌሎችን ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ ነው። እንዲህ ያለው በራስ ወዳድነት የታጠረ አስተሳሰብ ነው ለዘመናት የአገራችንን ሕዝብ ሲያንገላታና ሲያሰቃይ የኖረው።  ይህ ሁሉ ይሁን እንበልና “አማራ ገዝቷልና … ” በሚለው ሃሳብ እንኳን ብንሄድ  ለዚህ ነው ይህ አስተሳሰብ ከሞራል አኳያ የዘቀጠ ነው ያልኩት። ከዘራችሁ ሳጥን ወጥታችሁ፤ ይህ ተደርጎብናልና ይህንን እናደርጋለን ከሚል ጠባብነት ተላቅቃችሁ ለሰብዓዊነት መቆም ዋንኛ መመሪያችሁ ብታደርጉ ራሳችሁንና መጪውን ትውልድ ታተርፋላችሁ። እናንተም ብቻ ሳትሆኑም ሌሎችም በዘርና በጎሣ የጠበቡ ሁሉ ይህንን ሊያስተውሉትና ሊገነዘቡት ይገባል።በዚህ ሥር የሚጠቀሱት በአገሪቷ የሚካሄደውን አድሏዊነት ሽምጥጥ አድርገው የሚክዱ ናቸው። እስቲ በየክልሉ ያለውን ልዩነት እንመልከትና ራሳችሁ ፍርድ ስጡ። እጅግ በጣም ጥቂቱን ልጥቀስ።ዓለምአቀፋዊ የልማት ፕሮጀክቶች በቅድሚያ እንዲሄዱ የሚደረግበትየኤፈርት ዋና ጽ/ቤት የሚገኝበትና በቅርቡ ዊኪሊክስ (ሹልክዓምድ) እንዳጋለጠው ለኢትዮጵያ ተብለው ለሚሰጡ ዓለምአቀፋዊ ዕርዳታዎችንና ድጎማዎችን ኤፈርት ለትግራይና ለህወሃት እንዲውሉ ያደረገበትና በሥሩ ያሉት ድርጅቶች በህወሃት ቁልፍ ሰዎችና ተባባሪዎቻቸው ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ለትግራይ ክልል የተለየ እንክብካቤ የሚከናወንበትየኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጣን ዘጠና ስድስት በመቶ የሚሆነው በትግሬዎች ከመያዙ በላይ ወታደራዊ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤታቸው ያደረጉበትትግሬዎች ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስት በመቶ አካባቢ ሆነው ክልሉ ግን ከየትኛውም ክልል በበለጠ ሁኔታ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የተከማቹበት መሆኑበአገሪቷ ብቸኛ የቴክኖሎጂ ተቋም ያለበት፤ ከሚወጡ መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በዚህ ተቋም ለመግባት ትግሬ መሆን ወሳኝነት ያለው እንዲሁም በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ያለውን አሠራር ለመቆጣጠር ተማሪዎቹ ከትግሪኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛ የሚናገሩ እንዲሆን መደረጉ እንዲሁም የተቋሙ በር ጠባቂዎች የቀድሞ ተመራቂዎች እንዲሆኑ በማድረግ በአገሪቷ ውስጥ ምንም ዓይነት ተቋም ተፎካካሪው እንዳይሆን የተደረገበት ክልል መሆኑበመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከዚሁ ክልል የመጡበት መሆኑኢህአዴግ ብላችሁ በፈጠራችሁት ድርጅት ውስጥ የትግራይ ክልል ሕዝብ ከበርካታዎቹ ጋር ሲነጻጸር አናሳ ሆኖ ሳለ ከአማራውና ከኦሮሞው ድርጅት ጋር በመሆን በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ትግራይ ብቸኛ ተወካይነት እንዲኖረው የተደረገበትና ሌሎቹ በደቡብ ስም የተጠቃለሉበት የተቀሩት አምስት ክልሎች ከነጭራሹም ያልተወከሉበት አድሏዊነት በግልጽ የሚታይበት ክልል ነው።ለመሆኑ ህወሃት/ኢህአዴግ በዘር ላይ የተመሠረ አፓርታይዳዊ ሥርዓት ነውን?ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በኢትዮጵያ ያሉትን ዋንኛ ተቋማት ማን እንደሚቆጣጠር መመልከቱ በቂ ይመስለኛል። ዝርዝሩ እዚህ ላይ ይገኛል (http://www.solidaritymovement.org/downloads/140731-leaders-key-institutions-in-Ethiopia.pdf) እስቲ ተመልከቱትና ለራሳችሁ ወስኑ! እንደምትሉት በእውነት ኢትዮጵያ “የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠባት” ነች ወይስ የ-ተ-ረ-ጋ-ገ-ጠ-ባ-ት ነች? ከእነዚህም ሌላ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች፣ … በትግሬዎች፣ በህወሃት አባላት፣ በህወሃት ደጋፊዎች፣ … በሞኖፖል የተያዙ ናቸው። እንደሚታወቀው ነጻ የሆኑ ተቋማት በአንድ ነጻና የተረጋጋ ማኅበረሰብ ውስጥ ወሳኝነት ያላቸው ናቸው። ከዚህ አንጻር እንደነዚህ ያሉ ድርጅቶች ብቃት ባላቸውና ነጻ በሆኑ ግለሰቦች መመራታቸው ከአድልዖ የጸዱ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በአምባገነን ሥርዓቶች ግን እንዲህ ያሉትን ተቋማት በሥልጣን ባሉት ጥቂት ግለሰቦች ወይም በተላላኪዎቻቸው እንዲያዙ በማድረግ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማስረዘም የሚጠቀሙበት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው።  እንዲህ ያሉት ዘረኛ ጥቅመኞች ለሚከፍሉት ታማኝነት በምላሹ ከፍተኛ ሥልጣን፣ ሹመት፣ ዕድልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንዲያገኙ ይደረጋሉ።  ይህንን ጽሁፍ (http://www.solidaritymovement.org/downloads/140731-leaders-key-institutions-in-Ethiopia.pdf) ብትመለከቱ በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን ተቋማት ማን እየመራቸው እንደሆነና ከየትኛው ዘር እንደሆነ በግልጽ ልትመለከቱት ትችላላችሁ።  በዚህ ነጥብ ላይ የምለምናችሁ ነገር የለም። ከእነዚህ የዘመናት በሽታዎች ብትላቀቁ ራሳችሁንና መጪውን ትውልዳችሁን ታድናላችሁ። ከኅሊና ፍርድ ነጻ ትሆናላችሁ።  ለእናንተና ለዘራችሁ ግን ብዙ እጅግ ብዙ የምታጡት አለ።  ከዚህ ሌላ በፍጹም መዘንጋት የሌለባቸው አሉ።  ከትግራይ ማኅበረሰብ በርካታዎች እናንተ የምታደርጉትን አፓርታይዳዊ የዘር ፖሊሲ እንደሚቃወሙ አምናለሁ፤ ነገር ግን በገሃድ ወጥተው ለመቃወም እንደሚፈሩ አስተውላቸኋለሁ። እንዲሁም ከተለያዩ ክፍሎች የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ራሳቸውን በማነጽ ለልጆቻቸውና ለመጪው ትውልድ መልካም ለማድረግ የሚነሱትን ትግሬዎች መደገፍ እንደሚገባችሁ ላሳስብ እወዳለሁ።  ከፈጣሪ የተሰጠንን ልዩ መብት የምታከብር አገር ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትኖረን ውይይቱ ይጀመር።  ስለዚህ ሁላችንም እንደ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ተከባብረንና ተሳስበን ለመኖር የምንችልባት አገር ለመሥራት እንትጋ።   ስለዚህ እናንተም በህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያላችሁ ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ ልትሉት ትችላላችሁ፤ አላወቅንም ማለት ግን በጭራሽ አትችሉም። ህወሃትን ለምትቃወሙ የትግራይ ወንድሞችና እህቶቻችን፤ለስኬት ለመብቃት እና ህወሃት ለ23 ዓመታት የመሠረተውን የጥላቻና የዘር ግምብ ለማፍረስ ጠለቅ ያለ ከልብ የሆነ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል።  ስለዚህ ይህንን የህወሃት ፖሊሲ የማትደግፉ ከሆነ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ  ማለት አለባችሁ።እውነትን በቤታችሁንና በትናንሽ ቡድኖቻችሁ ውስጥ ሳይሆን በገሃድ የምትናገሩበት ጊዜ አሁን ነው።  ስለዚህ   ልትግባቡና ልትተማመኑ በምትችሉበት መንገድ በመነጋገር አንድ አቋም ላይ መድረስ አለባችሁ። ማኅበራሰባችሁን ማነጋገርና ማሳመን የእናንተ ቀዳሚ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል። መተማመንን ማዳበር የምትችሉት እናንተ ናችሁ። ከዚያም ከሌሎች ጋር ለመነጋገርና ለመወያየት በር እየተከፈተ ይሄዳል። የዕርቅ መሠረትንም መዘርጋት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስችላል።  ስለዚህ ከእናንተም የሚጠበቀው ከትግራይ ወገኖች ከሚጠበቀው ያነሰ አይደለም። ይህንን ግልጽ ደብዳቤ በራሴና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ስም ልኬላችኋለሁ። ከሰከራችሁበት የዘር ፖለቲካ የምትነቁ ከሆነ በጣም ጥቂት የሆነውን በዚህ ደብዳቤ ለማስፈር ሞክሬአለሁ። መልሳችሁን እጠብቃለሁ።አክባሪ ወንድማችሁ፤
ዋና ዳይሬክተር፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
አድራሻ፡ 910- 17th St. NW, Suite 419.
Washington, DC 20006 USA
Email: Obang@solidaritymovement.org.  Website: www.solidaritymovement.org  ለጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለኢህአዴግ፣ ለኦህዴድ፣ ለብአዴን፣ ለደኢህአዴን እና ለህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለኢትዮጵውያን የሲቪክና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ በዳያስፖራ ለሚገኙ ድርጅቶች፣  ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጆን ኬሪ፣ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሱዛን ራይስ፣ ምክትል የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በስትራቴጂክ ግንኙነት ዘርግ ቤን ሮድስ፣ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር የዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ሠራተኞች ጉዳይ ረዳት ጸሃፊ ቶም ማሊኖውስኪ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ም/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዳይሬክተር ግራንት ሃሪስ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ም/ቤት የልማትና የዴሞክራሲ ከፍተኛ ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ፣ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት ጸሃፊ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ ለዩኤስ ኤይድ ረዳት አስተዳዳሪ ኧርል ጋስት፣ በአሜሪካ ሕግመወሰኛ ምክርቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሮበርት ሜኔንዴዝ፣ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ከፍተኛ አባል ቦብ ክሮከር፣ በሕግ መወሰኛ ም/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስቶፈር ኩንስ፣ ለሌሎች የሕግ መወሰኛ ም/ቤት ከፍተኛ አባላት (ሴናተሮች) ሚች ማኮኔል፣ ዳያን ፋይንስታይን፣ ጆን ማኬይን፣ ሪቻርድ ደርቢን፣ ኤድዋርድ ሮይስ፣ በእንደራሴዎች ም/ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስቶፈር ስሚዝ፤ ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ለአውሮጳ ማህበር የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር፣ ለጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ለኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለአውሮጳ ኅብረት፣ ለአውሮጳ ኮሚሲዮን፣ ለካናዳ መንግሥት፣ ለታላቋ ብሪታኒያ መንግሥት፣ ለካናዳ ዓለምአቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ሲዳ)፣ ለአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ተቋም (ዩኤስኤይድ)፣ ለእንግሊዝ ዓለምአቀፍ ልማት መምሪያ፣ ለጃፓን የዓለምአቀፍ ትብብር ባንክ፣ ለጃፓን ዓለምአቀፍ ትብብር ኤጀንሲ፣ ለቻይና ዓለምአቀፍ ትብብር ካውንስል፣ ለህንድ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ፣ ለህንድ ኤግዚም ባንክ፣ ለቻይና ኤግዚም ባንክ፣ ለዳኒሽ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዳኒዳ)፣ ለፊንላንድ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር (ፊኒዳ)፣ ለፈረንሣይ ዓለምአቀፍ ትብብር መምሪያ፣ ለፈረንሣይ ልማት ኤጀንሲ፣ ለጀርመን ዓለምአቀፍ ልማት፣ ለኔዘርላንድስ የልማት ትብበር ሚ/ር፣ ለኖርዌይ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ኖራድ)፣ ለስዊድን ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር (ሲዳ)፣ ለስዊዝ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ፣ ለቱርክ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ)፣ Amnesty International, Human Rights Watch, International Commission of Jurists (ICJ), Physicians for Human Rights, The International Justice Resource Center (IJRC), The African Court of Justice and Human Rights, International Criminal Court (ICC), International Justice Project, United to End Genocide, Humanity United, Never Again Coalition, GlobalSolutions.org, The World Council of Churches (WCC), ACTION AID, AFRICA HERITAGE FOUNDATION, AFRICA LEGAL AID, AFRICAN DEVELOPMENT ASSOCIATION, ALLIANCE FOR FINANCIAL INCLUSION, BUSINESS ACTION AGAINST CORRUPTION, CARE INTERNATIONAL, CATHOLIC AGENCY FOR OVERSEAS DEVELOPMENT, CENTER FOR INTERNATIONAL PRIVATE ENTERPRISE, CORRUPTION WATCH, COUNCIL ON FOREIGN RELATIONS, CREATE TRUST, DEMOCRACY WATCH, FORD FOUNDATION, FREEDOM NOW, Free Africa Foundation, GENOCIDE WATCH, Global Advice Network, GLOBAL HUMAN RIGHTS DEFENSE, Global Integrity, INTERNATIONAL CRISIS GROUP, INTERNATIONAL LEGAL ALLIEANCE, Least Developed Countries Watch (LDC Watch), MELINDA & GATES FOUNDATION, Development Research Institute NYU, THE AFRICAN CHAMBER OF COMMERCE IN THE US, THE AFRICAN INSTITUTE OF CORPORATE CITIZENSHIP, The Bertelsmann Foundation, THE COMMONWEALTH BUSINESS COUNCIL, THE CORPORATE COUNCIL ON AFRICA, THE FINANCIAL ACTION TASK FORCE (FATF), THE GLOBAL CLEARINGHOUSE FOR DEVELOPMENT FINANCE, TRANSPARENCY INTERNATIONAL, TRUST Africa, U.K. Anti-Corruption Forum, Overseas Development Institute UK, OXFAM, PARTNERSHIP AFRICA CANADA, PAC, World Vision International, World Accord, HOPE International Development Agency, CARE- Cooperative for Assistance and Relief, Africa Governance Monitoring and Advocacy Project (AfriMAP), AFRICAN DEVELOPMENT BANK, AFRICAN UNION, The African Economic Community (AEC)-AU, Common Market for Eastern and Southern Africa (COMESA), East African Court of Justice (EAC), BANK FOR INTERNATIONAL SETTLEMENTS,ECONOMIC COMMISSION FOR AFRICA (ECA), INTERNATIONAL FUND FOR AGRICULTURAL DEVELOPMENT (IFAD), INSTITUTE FOR INTERNATIONAL COOPERATION AND DEVELOPMENT (IICD), Multilateral Investment Guarantee Agency-World Bank, INTERNATIONAL BANK FOR RECONSTRUCTION AND DEVELOPMENT WORLD BANK, International Monitory Fund (IMF), INTERNATIONAL LABOUR ORGANIZATION, Investment Climate Facilities for Africa Trust (ICF), ORGANIZATION FOR ECONOMIC CO-OPERATION AND DEVELOPMENT, Development Assistance Group (DAG), United Nations (UN)-Sectary, United Nations Human Rights Council, United Nations Development Programme (UNDP), United Nations Conference on Trade and Development (UNCTAD), Multilateral Investment Guarantee Agency, United Nations Industrial Development Organization UNIDO, Jeffrey Sachs (earth institute), Kofi Annan (Africa progress panel) ለአሜሪካ፣ ለታላቋ ብሪታኒያ፣ ለስዊድን፣ ለፈረንሣይ፣ ለእስራኤል፣ ለዴንማርክ፣ ለፊንላንድ፣ ለሩዋንዳ፣ ለካናዳ፣ ለብራዚል፣ ለሕንድ፣ ለኬኒያ፣ ለጀርመን፣ ለጣሊያን፣ ለአውሮጳ ኅብረት፣ ለአውስትራሊያ፣ ለቱርክ፣ ለስዊትዘርላንድ፣ ለጃፓን፣ ለዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮሪያ፣ ለኢንዶኔዢያ፣ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ለኖርዌይ፣ ለታንዛኒያ፣ ለግብጽ፣ ለቤልጂየም፣ ለጅቡቲ፣ ለሱዳን፣ ለቻይና ፣ ለደቡብ አፍሪካ እና ለኔዘርላንድስ ኤምባሲ አምባሳደሮች። እነዚህም፡ Africa Confidential, Al Jazeera, BBC, the Guardian, New York Times, Washington Post, Wall Street Journal, Bloomberg News, MSNBC, CNN, INDIAN OCEAN NEWSLETTER, REUTERS AFRICA, The East Africa, Business Daily, African Review, Deutsche Welle Radio, VOA Amharic, VOA-English, ESAT, Addis Fortune, ለሪፖርተርና ለሌሎች በአገር ውስጥ እና በዳያስፖራ ለሚገኙ ድረገጾች፣ የራዲዮ ፕሮግራሞች፣ መጦመሪያዎች፣ ወዘተ።

No comments:

Post a Comment