Tuesday, September 9, 2014

ኢህአዴግ በአንድ አመት ውስጥ ለተለያዩ ዝግጅቶች ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱ ተሰማ

 ኢሳት ዜና :-በአለፈው አንድ አመት ውስጥ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለፓርቲው የፖለቲካ ስራ የሚጠቅም ከመንግስት ባጀት ከ900 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ማውጣቱን ምንጮች ገለጹ።

ለብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ ለባንዲራ ቀን፣ ለመከላከያ ቀን፣ ለተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የፖለቲካ ስልጠና፣ ከ100 ሺ በላይ ለሚሆኑ የኢህአዴግ አባላት ስልጠና፣ ለፖሊስ ሰራዊት የተሰጠው ስልጠና፣ እንዲሁም በተለያዩ ታሃድሶ የሚል ስያሜ በተሰጣቸው ስልጠናዎችና ስብሰባዎች ከመንግስት ባጀት እስከ 900 ብር ወጪ መደረጉን እስካሁን የተሰባሰቡት የወጪ ደረሰኞች እንደሚያሳዩ ምንጮች ገልጸዋል።

አንዳንድ ወጪዎችን ክልሎች ቢያወጡዋቸውም ፣ ወጪው ከመንግስት ባጀት የሚሸፈን መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች፣ አሃዙ ተጠቃሎ ሲታወቅ ወጪው ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ገዚው ፓርቲ ለራሱ የፖለቲካ ስራ በተለያዩ ሰበቦች ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ማውጣት መቀጠሉ፣ ታክስ ከፋዩ ህዝብ በተዘዋዋሪ መንገድ ሳይፈልግ ፓርቲውን እዲደግፍ እያደረገው መሆኑንና የአገሪቱ አጠቃላይ ኦዲተሮችም ይህን ወጪ እንደመንግስት ወጪ በመያዝ ፓርቲውን ተጠያቂ ለማድረግ እንዳልቻሉ ምንጮች አክለው ተናግረዋል።

በተለይ የብሄር ብሄረሰቦች ፣ የባንዲራ እና የመከላከያ ቀን በሚባሉት ዝግጅቶች የአንድ አካባቢ ሰዎች ተሰባስበው እነሱ በመሰረቱት የዝግጅት ኩባንያ ዝግጅት በማዘጋጀት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ የጠቆሙት ምንጮች፣ እነዚህ ሰዎች ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በፈጠሩት ሽርክና የተለያዩ ሃሳቦችን
እያመጡና እና እያስጸደቁ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በመመዝበር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ግንባሩ ከዚህ ቀደም ለኤች አይ ቪ ቫይረስና ለሌሎችም በሽታዎች መከላከያ የሚመጡ ፈንዶችን ሲጠቀም መቆየቱን ያስታወሱት ምንጮች፣ በተለይ ግሎባል ፈንድ የተባለው አለማቀፍ ለጋሽ ድርጅት ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረውን እርዳታ መቀነሱን ተከትሎ፣ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ የመንግስትን ባጀት በመጠቀም
የፖለቲካ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አንዳንድ ዝግጅቶች በመንግስት ስም እውቅና ቢሰጣቸውም ዋና ተልእኮዋቸው የኢህአዴግን አብዮታ ዲሞክራሲ

ፖሊሲ ማንጸባረቅ መሆኑን ምንጮች አያይዘው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment