Wednesday, March 28, 2018

በኢትዮጵያ በቅርቡ በተቋቋመው ወታደራዊ ዕዝ /ኮማንድ ፖስት/በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ሁለት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ተለቀቁ።

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 19/2010) በኢትዮጵያ በቅርቡ በተቋቋመው ወታደራዊ ዕዝ /ኮማንድ ፖስት/በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ሁለት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ተለቀቁ። ከሳምንት በፊት ከእስር የተለቀቁት የኦሕዴድ ባለስልጣናት የምስራቅ ወለጋ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። በወታደራዊ እዙ ታስረው የነበሩት የኦሕዴድ አመራሮች የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሃብታሙ ቦረና እንዲሁም የነቀምት ከተማ ከንቲባ አቶ ካባ ሁንዴ ናቸው። እነዚሁ ባለስልጣናት በኮማንድ ፖስቱ የታሰሩ በየአካባቢያቸው ተከስቶ ከነበረው የሕዝብ አመጽ ጋር በተያያዘ መሆኑ ይታወሳል። የኦሮሚያ ባለስልጣናት መያዛቸውን ተከትሎም የፓርላማ ተወካይ የሆኑ የኦሕዴድ ተመራጮች እስሩ አግባብ አለመሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። ከታሳሪዎቹ መካከል ያለመከሰስ መብት የነበራቸው የክልል ምክርቤት አባላት እንደነበሩ በመግለጽ የፓርላማ አባላቱ ተቃውመው ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን የምስራቅ ወለጋ ዞን አመራሮችን በመፍታት በርካታ የታሰሩ ወጣቶችንም የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት መልቀቁ ነው የተነገረው። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በርካታ ወጣቶች የኦሮሚያ ክልል መንግስታዊ መዋቅር አመራሮች ታስረው እንደሚገኙ ሪፖርተር ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment