Friday, March 23, 2018

አበበ ካሴ ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመበት ነው

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 14/2010)በአርበኞች ግንቦት 7 ስም ተከሶ በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኘው አበበ ካሴ ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመበት መሆኑን ገለጸ።
ከ2006 ጀምሮ 7 አመት ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው አበበ ካሴ በተፈጸመበት ኢሰብአዊ ድርጊት ሽንቱን መቆጣጠር እንደማይችል ገልጿል።
ከወልቃይት ማንነት ጋር በተያያዘ በእስር ቤቱ ሃላፊዎች አሁንም ድብደባ እየደረሰበት ነውም ተብሏል።
አበበ ካሴ በአርበኞች ግንቦት ሰባት ስም ከተወነጀለበት ክስ ሌላ በአማራ ክልል ፍርድቤትም ሌላ የቅጣት ውሳኔ እንደመጣበት ይናገራል።
በግንቦት ሰባት ስም በቀረበበት ክስ 7 አመት ሲፈረድበት በወልቃይት ማንነት ሰበብ በተወነጀለበት ጉዳይ ደግሞ 20 አመት
እንደተፈረደበትም ነው የተነገረው።
አበበ ካሴ በማዕከላዊ እስር ቤት በነበረበት ወቅት በደረሰበት ድብደባም 20 የእግሩና የእጁ ጥፍሮች ሙሉ በሙሉ ተነቅለዋል።
ይህ ብቻ አይደለም በኤሌክትሪክ ንዝርት በተፈጸመበት ጉዳትም የዘር ፍሬው መምከኑን ገልጿል።
በግብረሰዶም ወንጀል ከተፈረደባቸውና ከአእምሮ ህሙማን ጋር ከአንድ አመት በላይ አንድ ላይ እንድታሰር ተደርጌያለሁ ማለቱም ታውቋል።
አበበ ካሴ በጓደኛው ዳንኤል ተስፋዬ በኩል እንደተገለጸው በደረሰበት ኢሰብአዊ ድርጊት ኩላሊቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብታል።
በዚህም ሳቢያ ሽንቱን መቆጣጠር እንደማይችልና ሕክምናም እንዳላገኘም ተገልጿል።

No comments:

Post a Comment