Monday, March 19, 2018

10 ሺ የሚጠጉ የሞያሌ ከተማ ተፈናቃዮች ስደት መጠየቃቸውን ተመድ አስታወቀ

 (ኢሳት ዜና ማጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ/ም)
ኬንያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽነር ባወጣው ዘገባ፣ እስካሁን 9 ሺ 700 ስደተኞች ከኦሮም ክልል ሞያሌ ከተማ ተፈናቅለው ኬንያ ገብተዋል። ስደተኞቹ 13 ሰዎች በወታደሮች መገደላቸውን እንደተናገሩ ተመድ አስታውቛል። በላይነሽ ታደሰ የተባሉ የ2 ልጆች እናት ፣ ጎረቤታቸው ከትምህርት ቤት የወላጆች ስብሰባ ሲመለስ በጥይት መገደሉን፣ በማግስቱ ሌላ ጓደኛቸው ወደ ሱቅ ሲሄድ ምሽት ላይ አንቀው መግደላቸውንና በዚህም የተነሳ ለደህንነታቸው ሰግተው መሰደዳቸውን ተናግረዋል።
80 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን የገለጸው ድርጅቱ፣ 1 ሺ 500 የሚሆኑት ስደተኞች እድሜያቸው ከ5 አመታት በታች ነው ብሎአል። አንድ ከተወለደ 6 ቀን የሆነው ህጻን መሰደዱን እንዲሁም 600 እርጉዝ ሴቶች መኖራቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል። በሶማሪ እና ሶሎሎ በሚባሉ የሞያሌ አካባቢዎች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች አፋጣኝ የሆነ ምግብ፣ ውሃ፣ የመጸዳጃ አገልግሎት፣ መጠለያና የህክምና ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል። ተመድ ብርድ ልብስ፣ ሳሙና፣ ጄሪካን፣ የማብሰያ እቃዎችንና የመሳሰሉትን ነገሮች አድሏል።
አብዛኞቹ ስደተኞች ሞያሌ ውስጥ በሚያውቋቸው ሰዎች ተጠልለው በመገኘታቸው የስደተኞችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ አለመቻሉንም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል። ባለፉት 2 አመታት ብቻ ከ700 ሺ በላይ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል።

No comments:

Post a Comment