Thursday, March 15, 2018

ሊቢያ በህገወጥ ሰው ማዘዋወር ስራ ላይ ተሰማርተዋል ባለቻቸው 250 ግለሰቦች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቷን አስታውቀች።

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2010) ሊቢያ በህገወጥ ሰው ማዘዋወር ስራ ላይ ተሰማርተዋል ባለቻቸው 250 ግለሰቦች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቷን አስታውቀች። ሊቢያውያንና ሌሎች የውጪ ዜጎች በተጠረጠሩበት በዚህ ወንጀል ከፍተኛ የደህንነት ሰራተኞች ፣ የመጠለያ ካምፕ ሃላፊዎች እና በሊቢያ የሚገኙ የኤምባሲ ሰራተኞች ተሳታፊ ናቸው ሲሉ የሊቢያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገልጸዋል። የሙሀመድ ጋዳፊን መውደቅ ተከትሎ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው ሊቢያ በህገጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ቶርቸርን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የሰብባዊ መብት ጥሰት እንደሚካሄድ ቢቢሲ ዘግቧል። በህገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ በባህር ለሚደረገው ጉዞ እንደመሸጋገሪያ የምታገለግለው ሊቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች የስቃይ መነሃሪያ መሆንዋን የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። እራሱን እስላማዊ እስቴት በማለት በሚጥራው ቡድን ይከናወናል በተባለው የባሪያ ንግድን ጨምሮ እንግልትና ግድያ በርካቶች ለስቃይ መዳረጋቸውን ከስፍራው በተደጋጋሚ ከሚወጡ ዘገባዎች ሲሰማ ቆይቷል። በጣሊያን መንግስት ድጋፍ በህገጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ
ተጀምሯል በተባለው በዚህ ዘመቻ ለ250 ተጠርጣሪዎች የሊቢያ መንግስት የእስር ማዘዣ መውጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል። በህገወጥ የሰው ዝውውር መስመር ውስጥ የእስላማዊ ታጣቂዎች እጅ እንዳለበት ደርስንበታል ያሉት የሊቢያ ጠቅላይ አቃቤህግ ሳዲቅ አልሱር፣ ሊቢያውያንንና ሌሎች የውጪ ዜጎች በተጠረጠሩበት በዚህ ወንጀል ከፍተኛ የደህንነት ሰራተኞች ፣ የስደተኛ መጠለያ ካምፕ ሀላፊዎች እና በሊቢያ ውስጥ የሚገኙ የኤምባሲ ሰራተኞችም በዚህ ወንጀል ተሳትፈዋል ብለዋል። በቀጣይ ተጠርጣሪዎቹን ወደ ህግ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረትም ይቀጥላል ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ በተለያዩ ታጣቂዎች በምትታመሰው እና እራሱን እስላማዊ ግዛት ብሎ በሚጠራው ቡድን ቁጥጥር ስር ያሉ ግዛቶች ባሉበት ሁኔታ አዘዋዋሪዎቹን ለህግ የማቅረቡ ሂደት አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጿል። ሲ ኤን ኤን በሰራው ዘጋቢ ፊልምና በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ለማየት እንደተቻለውም በዚህ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የባሪያ ፍንገላ ርምጃ ኢትዮጵያዊያንም ሰለባ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል። ራሱን አይሲሰ በሚለው አሸባሪ ቡድን የዛሬ 3 ዓመት 28 ኢትዮጵያዊያንም መገደላቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment