Wednesday, March 28, 2018

እነእስክንድር ነጋ ከነበሩበት የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ወደ እስር ቤት መወሰዳቸው ተሰማ

Image may contain: 8 people, people smilingእነእስክንድር ነጋ ከነበሩበት የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ወደ እስር ቤት መወሰዳቸው ተሰማ። ያልተፈቀደ ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋል በሚል የታሰሩት እነእስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ 48 ሰዓታት እንዳለፋቸውም ቤተሰቦቻቸው አስታውቀዋል። ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫ ያወጡት ዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጊቱን በማውገዝ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ፖሊስ ጉዳዩን ለኮማንድ ፖስት አሳውቄ ምላሽ እየተጠባበኩ ነው ማለቱም ተገልጿል። ኮከብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋል ተብለው የታሰሩት እነእስክንድር ነጋ ክስ ሳይመሰረትባቸው ቀናት ተቆጥረዋል። ዕሁድ ዕለት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት መኖሪያ ቤት በተደረገው ፕሮግራም ላይ የተሳተፉት ጋዜጠኞች፣ጦማሪያውያንና የፖለቲካ መሪዎች ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ጊዜ አልፏል። በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት ከነበሩበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት ወደ መደበኛ እስር ቤት ዛሬ መግባታቸውንም ከቤተሰብ አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አሁን ያሉበት ሁኔታ ከባድ እንደሆነም ተገልጿል። በአንድ ክፍል ውስጥ 90 የሚሆኑ እስረኞች በሚገኙበት ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ነው ለማወቅ የተቻለው። ክፍሏ ከመጥበቧ የተነሳ ለመኝታ የሚሆን ቦታ ባለመኖሩ ቆሞ ለማደር መገደዳቸውን ቤተሰብ ገልጿል። እስክንድር ነጋን ዛሬ ያነጋገሩ ሰዎች እንደገለጹት እስረኞቹ ያሉበት ሁኔታ ለጤንነታቸው በጣም አስጊ ነው። ‘’መስማት ለሚፈልግ፣ ወይም ለሚሰማ ሰው ሁሉ
ንገሩልን። ያለንበትን ሁኔታ የሚገልፀው ኢሰብአዊ የሚለው ቃል ነው” በማለት እስክንድር መናገሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በአንድ ክፍል ውስጥ ታስረው የሚገኙት በአብዛኛው ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በተያያዘ የታሰሩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን እነእስክንድርም ጉዳያቸው በዚሁ ኮማንድ ፖስት ስር እንዲታይ ለማድረግ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። የፖሊስ ጣቢያው አዛዥ ጉዳዩን ለኮማንድ ፖስቱ በማሳወቃችን ምላሽ እየጠበቅን ነው ማለታቸውም ተጠቅሷል። ይህም የእነእስክንድርን እስር የሚመለከተው መደበኛው ፖሊስ ሳይሆን ኮማንድ ፖስቱ መሆኑን የሚያመላክት ነው ተብሏል። ኮማንድ ፖስቱ እስከአሁን በጉዳዩ ላይ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ መግለጹ የሚታወስ ነው። አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፔን አሜሪካ፣ ሲፒጄና አይ ፒ አይ እስረኞቹ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል። የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ የታሰሩበትን ምክንያት በማጣጣል ማንም ሰው የፈለገውን ሰንደቅ አላማ በቤቱና በግቢው ውስጥ መስቀል ወንጀል አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል። ኮከብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋላ ተብለው ከዕሁድ ጀምሮ የታሰሩት ተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንደር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ በፍቃዱ ሀይሉ፣ አዲሱ ጌትነት፣ ወይንሸት ሞላ፣ ይድነቃቸው አዲስና ተፈራ ተስፋዬ መሆናቸው ታውቋል።

No comments:

Post a Comment