Monday, March 19, 2018

ኤርትራ በኢህአዴግ የቀረበባትን ክስ አጣጣለች

 (ኢሳት ዜና ማጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ/ም) ኤርትራ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እያደረገች ነው በማለት በህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ በኩል የቀረበውን ክስ፣ ኤርትራ አጣጥላዋለች። “ኢትዮጵያ ችግሩን ውጫዊ ለማድረግ ከመፈልግ ይልቅ፣ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ተቃውሞውና አለመረጋጋት ለመፍታት ብትሰራ ይሻላታል” ስትል ገልጻለች። የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ መስቀል ለብሉምበርግ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለውስጣዊ ችግሩ ውጫዊ ምክንያት እየፈለገ፣ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ እየሞከረ ነው ብለዋል። የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሰፋ አብዩ በቅርቡ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያዎች እና እስከ 20 ሺህ የሚጠጉ ጥይቶች መያዛቸውን ገልጸው ነበር። የውጭ ሀይሎች በሀገር ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በጦር መሳሪያ ለመደገፍ ይፈልጋሉ ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረው ነበር። የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልም እንዲሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከኤርትራ የሚነሱ ሃይሎችን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ተናግረው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የሚታዬው ተቃውሞ በአስተዳደር ፣ በዲሞክራሲ እና በፍትህ እጦት የመጣ መሆኑን ኢህአዴግ በተደጋጋሚ በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ራሰን ወታደራዊ እዝ ብሎ የሾመው ቡድን ጸሃፊ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በኢትዮጵያ የሚታዬው ተቃውሞ “የቀለም አብዮት” መልክ አለው በማለት ለችግሩ ምዕራባውያናንን ተጠያቂ ለማድረግ ሞክረው ነበር። በኤርትራ ላይ የቀረበው ክስ አዲስ ባይሆንም፣ ኢህአዴግ ለውስጥ ችግሩ ውስጣዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ውጫዊ ምክንያቶችንና ውጫዊ መፍትሄዎችን ለመፈለግ መጣሩ፣ አገዛዙ የፖለቲካ መፍትሄ ለማምታት አለመዘጋጀቱን የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል።

No comments:

Post a Comment