Wednesday, March 28, 2018

እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በርካታ ዜጎች ተጨናንቀው በሚገኝበት ክፍል ውስጥ መግባታቸው ታወቀ

(ኢሳት ዜና ማጋቢት 19 ቀን 2010 ዓ/ም) ወታደራዊ እዙን ሳታስፈቅዱ ስብሰባ አድርጋችሁዋል፣ አርማ የሌለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተጠቅማችሁዋል በሚል ሰበብ በእስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች ፣ ጎተራ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንዲታሰሩ መደረጉ ታውቋል። የመብት ተሟጋቾቹ በተያዙ በመጀመሪያው ቀን ከ90 በላይ ሰዎች ተጨናንቀው በሚገኙበት ክፍል ውስጥ እንዲታሰሩ ከተደረገ በሁዋላ፣ በማግስቱ ተለይተው በአንድ ቢሮ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጅ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ወደ መጀመሪያውና አስከፊ ወደ ተባለው ክፍል እንዲገቡ ተደርጓል። እስረኞቹን እስካሁን ለፍርድ ያቀረባቸውም ሆነ ያነጋገራቸው አካል የለም። ባለፈው እሁድ ጀሞ በሚባለው አካባቢ በቅርቡ ከእስር ለተፈቱት ሰዎች በተዘጋጀ የምስጋና ዝግጅት ላይ በመገኘታቸው የታሰሩት፣ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሃይሉ፣ ጸሃፊ ዘላላም ወርቃገኘሁ፣ ይድነቃቸው አዲስ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አዲሱ ጌታነህ፣ ተፈራ ተስፋዬ፣ ማህሌት ፋንታሁንና ወይንሸት ሞላ ናቸው። እንዲሁም በባህርዳር ለወታደራዊ እዙ ሳያሳውቁ ስብሰባ አድርገዋል የተባሉ ከ19 ያላነሱ ምሁራን ፣ ጋዜጠኞችና የህግ ባለሙያዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ። እስረኞቹ አዋጁን በመተላለፍ ለወታደራዊ እዙ ሳያሳውቁ ስብሰባ አድርገዋል በሚል በ9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ምርመራ ሲደረግባቸው ነበር። በእስር ላይ ከሚገኙት ወጣት ምሁራን መካከል ፣በባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚዳንትና ተመራማሪ፣ አቶ ጋሻው መርሻ፣ የሱፍ ኢብራሂም፣ ተመስገን ተሰማ፣ በለጠ ሞላ፣ የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ፣ ጋዜጠኛ በለጠ ካሴና ኢንጂነር ሲሳይ አልታሰብ ይገኙበታል።

No comments:

Post a Comment