Friday, March 23, 2018

የአማራ ክልል የሕዝብ ቁጥር እድገት እጅግ አዝጋሚ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 14/2010) የአማራ ክልል የሕዝብ ቁጥር እድገት እጅግ አዝጋሚ መሆኑን በኢትዮጵያው አገዛዝና በአለም አቀፍ ለጋሾች የቀረበ አንድ ሰነድ አመለከተ።
በዚህ ሰነድ መሰረት በመጪው የሕዝብ ቆጠራ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተጨማሪ 3 ሚሊየን የአማራ ህዝብ ሊጠፋ እንደሚችል ተገምቷል።
በሰነዱ እንደተመለከተው ለምግብ እጥረት የተጋለጡትን ለመለየት በተካሄደ የሕዝብ ቁጥር ትንበያ ጥናት የአማራ ክልል ነዋሪዎች 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ብቻ ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ደግሞ 36. 5 ሚሊዮን መሆን ቢኖርበትም በሁለት ሚሊዮን ቀንሶ 34.5 ሚሊዮን መሆኑ በሰነዱ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የሕዝብና የቤት ቆጠራ የተካሄደው በ1999 ከ11 አመታት በፊት ነበር።
በሃገሪቱ ሕገ መንግስት የሕብና የቤት ቆጠራ በየ10 አመቱ መካሄድ ቢኖርበትም ሕጉ ተጥሶ ይህ ሳይደረግ ከ1 አመት በላይ አልፎታል።
በሕገመንግስቱ መሰረት ቢሆን ኖሮ የሕዝብና ቤት ቆጠራው 10 አመቱን ጠብቆ በ2009 ሊካሄድ ይገባ ነበር።

ይህም ሆኖ ግን በሃገሪቱ ያለው አገዛዝ ለእርዳታ አሰጣጥ ያመች ዘንድ ከለጋሽ ሃገራት ጋር ባካሄደው የሕዝብ ቁጥር ትንበያ ጥናት መሰረት የአማራ ክልል ሕዝብ 20 ነጥብ 7 ብቻ ነው ተብሏል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የሕዝብ ቁጥር እድገት በየአመቱ በ2 ነጥብ 8 በመቶ ይሆናል።
በዚህም መሰረት በሕዝብ ቆጠራ ጥናት ትንበያው የአማራ ክልል ሕዝብ 23 ሚሊዮን መሆን ነበረበት ይህም በ1999 ከነበረው 17 ነጥብ 2 ሚሊየን የአማራ ክልል ሕዝብ ቁጥር በ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብቻ ጨምሮ አዝጋሚ እድገት ማሳየቱ ነው የተነገረው።–አሁን የተተነበየው 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ብቻ ነውና።
የአማራ ሕዝብ ቁጥርን ለመግታት ሆን ተብሎ ሴቶች እንዳይወልዱ በማድረግ እንዲሁም የዘር ማጥፋትን እየተካሄደበት ነው በሚል የመብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
ለዚህም መነሻ የሚያደርጉት በ1999 በተካሄደው ቤት ቆጠራ የአማራ ሕዝብ ቁጥር ከተገመተው በ 2 ሚሊዮን መቀነሱ በይፋ በፓርላማ መነገሩን ተከትሎ ነው ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ቁጥር 34 .5 ሚሊየን ብቻ መሆኑም በሰነዱ ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ 36. 5 ሚሊዮን መሆን ቢኖርበትም በሁለት ሚሊዮን ቀንሶ 34.5 ሚሊዮን መሆኑ በሰነዱ ሰፍሯል።
በዚህ ሰነድ መሰረት በ1999 26 ነጥብ 9 ሚሊየን የነበረው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ በ7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሲጨምር የአማራ ክልል ሕዝብ በ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ጨምሯል።
ከዛሬ 11 አመት በፊት በ1999 በተካሄደው ቆጠራ 2 ሚሊየን የአማራ ሕዝብ ጠፋ መባሉ አይዘነጋም።
የጠፋው ሕዝብ ሳይገኝ ከ 10 ዓመት በኋላም ዘንድሮ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር መቀነሱ የሚያመለክት ሰነድ መውጣቱ ቁጣ ሊቀሰቅስ እንደሚችል የሰነዱ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment