Friday, March 2, 2018

122ኛው የአድዋ የድል በአል በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችና ኢትዮጵያን በሚኖሩበት የተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በአሉ በድምቀት ተከብሮ ዋለ።

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 23/2010) በተለይ በአዲስ አበባ የነበረው አከባበር እጅግ ደማቅና ከሌላው ጊዜ የተለየ እንደነበር በምስል ተደግፎ ከተሰራጨው መረጃ መረዳት ተችሏል። የጣሊያን ወራሪ ሃይልን ለመመከት በአጼ ሚኒሊክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር የዛሬ 122 አመት አድዋ ላይ ኢትዮጵያን ነጻ አውጥቷል። ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ወደ አድዋ ጦር ግንባር ሲጓዙም በጀግንነታቸው ዘወትር የሚነሱትን ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱን በማስከተል ነበር።–ጣይቱ በዛን ወቅት ጀግና ለመሆን ቆራጥነት እንጂ ወንድ ሆኖ መፈጠር አይጠይቅም በሚለው የጀግና አባባላቸውም ይታወቃሉ። ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ የጣሊያን ጦርን ድል ነስተውና አሳፍረው ከመመለሳቸው ባለፈም ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ንጉስ እንደሆኑም የታሪክ መዝገቦች ያስረዳሉ። በዛን ዘመን የወፍጮ፣የስልክ፣የፓስታ፣የውሃ ቧንቧ፣ ቀይመስቀል፣ ሆስፒታል፣ ባቡር፣ባንክ፣ሆቴልና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያደረጉ ንጉስና የሀገር መሪ ነበሩ። ይህንን ታሪካቸውን ለመዘከርም በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶች በአሉ ወደሚከበርበት ስፍራ ሲጓዙም በዛን ወቅት የነበሩ አለባበሶችን፣ጌጦችንና የጀግንነት ማሳያ የሆኑትን ጋሻና ጦር በማያዝ ነው። ትላንት አያቶቻችንና አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬ
በነጻነት ቆመናል በማለት በተጓዙባቸው ጎዳናዎች ሁሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ወጣቶቹ የእግር ጉዞ በማድረግም በአሉ ወደሚከበርበት የአራዳ ጊዮርጊስ በማምረትም ለአጼ ሚኒሊክ ክብር በቆመው ሃውልት ፊት በመገኘት ምስጋናና አክብሮታቸውን ገልጸዋል። ለዚህች ሃገር በአንድነት መቆየት አሻራቸውን ያኖሩ አባቶችም በአደባባዩ በመገኘት በአሉን አብረው አክብረዋል። በተለያዩ የአለም ክፍል የሚገኙም ኢትዮጵያውያን በአሉን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል። በተለይም በማህበራዊ ድረገጾች ላይ በአሉን በማስመልከት የተለያዩ ታሪካዊ ጽሁፎች፣ምስሎችና በድምጽ የተደገፉ መረጃዎች በስፋት ተሰራጭተዋል። ዛሬ ላይ ቆመን በነጻነት ስለነጻነት የምንነጋገረው ትላንት አባቶቻችን በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት ነው ሲሉም ተደምጠዋል። በተመሳሳይ የአድዋ ጦርነት በተካሄደበት የሶሎን ተራራ ላይም በአሉ በድምቀት ተከብሯል።በአሉን ለማክበርም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ስፍራው ያቀኑት ሰዎችም የዛን ወቅት የሚያስታውሱ አልባሳታንና መፈክሮችን በማሰማት ለበአሉ ድምቀትን ሰጥተውታል። በበአሉ ላይ ለመታደምም ከአዲስ አበባ ጥር 7/2010 በእግራቸው ጉዞ የጀመሩትና ሶሎን ተራራ የደረሱት ጉዞ አድዋ የሚል ስያሜን ለራሳቸው የሰጡት ወጣቶችም ሌላው የበአሉ አድማቂዎች ሆነዋል።

No comments:

Post a Comment