Thursday, March 1, 2018

በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመልከታቸውን አቶ ኦኬሎ አኳይ ተናገሩ

(ኢሳት ዜና የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ/ም)የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ በቅርቡ ከእስር ቤት ተፈተው ኖርዌይ ገቡ በሁዋላ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በእስር ቤት ውስጥ ብልታቸው የተኮላሸ፣ በድብደባ ብዛት መራመድ የማይችሉ እንዲሁም በደረሰባቸው ጥቃት ራሳቸውን ስተው ያበዱ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። በአርበኞች ግንቦት7 አባልነት ተከሶ በእስር ላይ የሚገኘው አበበ ካሴ ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ብልቱ ላይ በደረሰበት ድብደባ በደም ተጨማልቆ መምጣቱን ማየታቸውን የተናገሩት አቶ ኦኬሎ፣ በእርሳቸውና አብረዋቸው በታሰሩ ሌሎች ጓደኞቻቸውም ላይ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ በተለይ ቃሊቲ በነበሩበት ወቅት በደረሰባቸው ድብደባ የተጎዳውን አካላቸውን ኖርዌይ ውስጥ ለመታከም እየሞከሩ መሆኑ ገልጸዋል። ከደቡብ ሱዳን በአገዛዙ ደህንነቶች ታፍነው ከተወሰዱት በሁዋላ የኖርዌይ መንግስት የእርሳቸውን ደህንነት ለማወቅ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ የእስር ቤቱ ባለስልጣናት “ የለም” የሚል መልስ መስጠታቸውን የገለጹት አቶ ኦኬሎ፣ ይሁን እንጅ በድብቅ አሾልከው የጻፉት አጭር ማስታወሻ የኖርዌይ ኢምባሲ ሰራተኞች እጅ በመግባቱ አድራሻቸው ሊታወቅ መቻሉን ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የአገዛዙ ባለስልጣናት በህዝብ ላይ የሚፈጽሙት ጭፍጨፋ በማንሳት በእስር ቤት ውስጥ ተቃውሞ ያሰሙ እንደነበር የገለጹት አቶ ኦኬሎ ፣ ቂሊንጦ ውስጥ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና ጨለማ ቤት እንዲገቡ መደረጉን አውስተዋል። ከእርሳቸው ጋር ከታሰሩት መካከል ያልተፈቱ ሰዎች መኖራቸውንም አቶ ኦኬሎ ተናግረዋል። አቶ ኦኬሎ እስር ቤት በነበሩበት ጊዜም ሆነ ከእስር ቤት ከወጡ በሁዋላ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኖርዌይ መንግስትና በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ከአቶ ኦኬሎ አኳይ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ሙሉውን በድረገጻችን ላይ መከታተል የምትችሉ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን።

No comments:

Post a Comment