Tuesday, March 6, 2018

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠራው አድማ እንደቀጠለ ነው

Image may contain: one or more people, sky and outdoor(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2010) በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠራው አድማ በኦሮሚያ ክልል ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።
አዲስ አበባ ዙሪያን ጨምሮ በምዕራብ ሸዋ፣ በወለጋ፣ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በምስራቅ ሀረርጌ፣ በባሌና በአርሲ ለሶስት ቀናት የተጠራው አድማ ተጠናክሮ መቀጠሉን ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች አመልክተዋል።
ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ ከተሞች የሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ተቋርጧል። በሆለታ አንድ ወጣት በአጋዚ ወታደር በጥይት መመታቱ ታውቋል።
በመቱ አቅመ ደካማ ለሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የዕለት ምግብ እንዲደርሳቸው በመደረግ ላይ ነው። ከሞያሌ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው ዋናው መስመር ከዝዋይ በኋላ መዘጋቱንም ለማወቅ ተችሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወምና የቀሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ በሚል የተጀመረው የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በሁለተኛ ቀንም የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በማቆም ቀጥሏል።
ከወለጋ ነቀምት ጊምቢ፣ ደምቢዶሎ፣ ነጆና ቄሌም ወለጋ አድማውን በተጠናከረ ሁኔታ ለሁለተኛ ቀን ካስተናገዱ ከተሞች የሚጠቀሱ ናቸው።
በተቃጠሉ ጎማዎች በርካታ መንገዶች ተዘግተው የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎል ማድረጋቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ምዕራብ ሸዋም እንዲሁ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ለሁለተኛ ቀን ባደረጉት አድማ ማንኛውንም ዓይነት የንግድም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዲቆም አድርገዋል።
በተለይም በቡራዩ፣ በሰበታ፣ ዓለም ገና፣ ፉሪና ወለቴ ጠንከር ያለ የአድማ እንቅስቃሴ እንደሚታይባቸው መረጃዎች አመልክተዋል።
በሆለታ አንድ ወጣት በአጋዚ ወታደር በጥይት መመታቱ የተገለጸ ሲሆን ከባድ ጉዳት እንደደረሰበትም ለማወቅ ተችሏል።
በምዕራብ ኢትዮጵያ ጅማ፣ መቱ፣ ቡኖ በደሌ አጋሮና ሌሎች ከተሞች በአድማው ተሳታፊ ሆነው ቀጥለዋል።
በመቱ ለጉልበት ሰራተኞችና አቅመ ደካሞች እንዳይራቡ በሚል ወጣቶቹ ዛሬ የምሳ ግብዣ እንዳደረጉላቸው ለኢሳት በምስል ተደግፎ ከደረሰው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እስከሞያሌ ድረስ ባለው መንገድ የአድማው እንቅስቃሴ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
መቂ ላይ መንገድ በመዘጋቱ ከሞያሌ አዲስ አበባ ባለው መስመር በሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠሩ ታውቋል።
መንገደኞች ከአንድ ቀን በላይ መንገድ ላይ ለማደር እንደተገደዱም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በያቤሎ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን በሂዲሎላም አድማው የንግድ ቦታዎችን ከእንቅስቃሴ ውጪ እንዳደረጋቸው ተገልጿል።
በምዕራብና በምስራቅ ሀረርጌም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ አድማው ለሁለተኛ ቀን ቀጥሏል።
ገለምሶና ጭናቅሰን ትላንት አድማውን ከጀመሩት ጋር ተቀላቅለዋል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች መንገድ በመዝጋት ሀገር አቀፉን አድማ በመቀላቀል ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዛሬ ከጎንደር ወደ መተማ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱ ታውቋል።
ከጎንደር ጭልጋ፣ ነጋዴባህር መተማ ሱዳን መስመር ያለው መንገድ በመዘጋቱ በተለይ ነዳጅ በሚያመላልሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠሩን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በደቡብ የኢትዮጵያ ከተሞች ህዝቡ ለተቃውሞ እንዲነሳ ጥሪ እየቀረበ ነው።
በወልቂጤ፣በሆሳዕናና ወራቤ እንደተጀመረው ሁሉ ሌሎችም በደቡብ ኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች ሀገራዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን እንዲቀላቀሉ ተጠይቋል።

No comments:

Post a Comment