Friday, March 23, 2018

ከ150 ያላነሱ በአብዛኛው የኮሎኔልነት ማዕረግ ያላቸው የጉምሩክ ሰራተኞች ከስራ ተቀነሱ

 (ኢሳት ዜና ማጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ከተቀነሱት ውስጥ 98 በመቶ የሚሆኑት የህወሃት ወታደሮች የነበሩ ናቸው። ብዙዎቹ የትምህርት ማስረጃቸው ብቁ አይደለም በሚል እንደተባረሩ ኢሳት ከደረሰው ደብዳቤ ለማወቅ ችለናል። ኢሳት ትናንት ባቀረበው ዘገባ በሶማሊ ክልል 38 የኮሎኔልነት ማዕረግ ያላቸው እና ከመከላከያ ወደ ጉምሩክ ተዛውረው ለ8 ዓመታት ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች መቀነሳቸውን ጠቅሶ ነበር። ከተቀነሱት መካከል 34ቱ የህወሃት ታጋዮች እንደነበሩም የጉምሩክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። ይሁን እንጅ ዛሬ ባገኘው የስም ዝርዝር ደግሞ ከሶማሊ ክልል ብቻ 101 ሰዎች ሲቀነሱ፣ ከሃዋሳና ሌሎች አካባቢዎች እስከ 150 ሰዎች ተቀንሰዋል። 90 በመቶ የሚሆኑት የመከላከያ አባላት ሲሆኑ፣ አብዛኞቹም የኮሎኔልነት እና የሻለቅነት ማዕረግ ያላቸው ናቸው። ዛሬ ከደረሰን የስም ዝርዝር መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ብሄር ተወላጅ የህወሃት ወታደሮች የነበሩ ናቸው። ከተቀነሱት መካከል ኢሳት አንዱን ነባር ታጋይ ያነጋገረ ሲሆን፣ ታጋዩ ከመከላከያ ወደ ጉምሩክ መወሰዱንና ለ8 ዓመታት በኦጋዴን አካባቢ ማገልገሉን ተናግሯል። ይሁን እንጅ አሁን በትምህርት ማስረጃ ስም ከስራ እንደተቀነሰ እንደተነገረውና ግራ እንደገባው ገልጿል። ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውንና መልስ በማጣታቸው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ አቤት ለማለት ማሰባቸውን ግለሰቡ አክሎ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment