Friday, March 2, 2018

በህገወጥ መንገድ አስቸኳይ አዋጁ በጸደቀበት ዕለት በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ መከሰቱ ተሰማ።

በአምቦ፣ በነጆ፣ በወሊሶና በአዲስ አበባ አስቸኳይ አዋጁን በመጣስ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በአዲስ አበባ ለአድዋ በዓል አደባባይ የወጡ ወጣቶች በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ የሚያወግዙ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ እንደነበር በቪዲዮ ተደግፎ ከመጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኪሎ በሚገኘው የፓርላማ ህንጻ በተሰበሰቡበት ሰዓት ፒያሳ ሚኒሊክ አደባባይ የአድዋ 122ኛ ዓመት መታሰቢያ በድምቀት ይከበራል። ከፓርላማው የተሰበሰቡት ተወካዮች በአስቸኳይ አዋጁ መጽድቅ ላይ ድምጽ ሲሰጡ; ከሚኒሊክ አደባባይ የተሰበሰቡት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደግሞ አዋጁ የሚከለክለውን ተቃውሞ የማሰማትን ገደብ ጥሰው በአገዛዙ ላይ የተቃውሞ ድምጽ እያሰሙ ነበር። ከፓርላማው ድምጽ ተገልብጦ ቁጥር ተጨምሮና የድምጽ ቆጠራው አወዛጋቢ በአሆነ መልኩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲጸድቅ በአድዋ በዓል መታሰቢያ የታደሙና አገዛዙ ላይ ጠንካራ የተቃውሞ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉት ወጣቶች በቤተመንግስት ደጃፍ በማለፍ ላይ ነበሩ። በመጨረሻም አዋጁ መጽደቁ ተነገረ። የአዲስ አበባ
ወጣቶችም ተቃውሟቸውን ቀጠሉ። በድምቀት በተከበረው በዛሬው የአድዋ በዓል ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች አስቸኳይ አዋጁ የሚጥለው ገደብን ጥሰዋል። ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ በሚል ዜማ የታጀበ የተቃውሞ መልዕክት የተሰማ ሲሆን ሌሎች ወቅቱን የሚገልጹ የተቃውሞ መፈክሮችም ተስተጋብተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአወዛጋቢ የድምጽ አቆጣጠር ውጤቱ ከተገለጸ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን መረጃዎች አመልክተዋል። በአምቦ የባጃጅ አሽከርካሪዎች የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው የተሰማ ሲሆን በቀጥታ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ማረጋጋጥ አልተቻለም። ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጠውን አስገዳጅ አንቀጽ የጣሰ ርምጃ በመሆኑ በተለየ ሁኔታ ተጠቅሷል። በወለጋ ነጆም በተመሳሳይ የአስቸኳይ አዋጁ በፓርላማ ጸደቀ መባሉን ተከትሎ ተቃውሞ መነሳቱን ለማወቅ ተችሏል። በነጆ የተካሄደው ተቃውሞ በመንግስት ተቋማት ላይ ርምጃ በመውሰድ የተካሄደ መሆኑ ታውቋል። ለኢሳት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ህዝቡ በፓርላማው የድምጽ ስርቆት ቁጣውን እየገለጸ ነው። የፓርላማ አባላቱ ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱም ከህዝቡ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment