Tuesday, October 7, 2014

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መንግስት በሚቀጥለው አመት በኤርትራ መንግስትና በተቃዋሚዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ ይወስዳል አሉ

ኢሳት ዜና :-
የመጨረሻ የስራ ዘመናቸውን ዛሬ ለጀመሩት የተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መንግስት አምና እንዳደረገው ሁሉ ዘንድሮም ከኤርትራ
መንግስት ለሚሰነዘር ማንኛውም ትንኮሳ ተመጣጣኝ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል። የኤርትራ መንግስት አስታጥቆ የላካቸውን የ ግንቦት7 ፣ ኦብነግና ኦነግ ጥቃቶችን መከላከላቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ አመትም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሙላቱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በዘረኝነትና በጥላቻ ተነሳሰስተው ተቃውሞ እንደሚያነሱም ገልጸዋል። መንግስት በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች ጉልበት የላቸውም እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቃታቸውን ሲመክት መቆየቱንና ተመሳሳይ እርምጃ በዚህ
አመትም እንደሚወስድ መግለጹ እርስ በርስ የሚቃረን መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ዶ/ር ሙላቱ መንግስት ለኤርትራ መንግስት ተደጋጋሚ የድርድር ጥያቄ ሲያቅርብ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት ለኤርትራ መንግስት ሲሰልሉ ተገኝተዋል በተባሉ ሶስት ኢትዮጵያውያን ላይ እንዲከላከሉ ወስኗል። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ጉለመዲ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ነጋሲ ብርሃነ ሹማይ፣ ተበጀ
በረኸ እና ብለጽ ገብረጻድቃን ዛላንበሳ ስለሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ለኤርትራ መረጃ ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ግለሰቦቹ ከኤርትራ መንግስት ስልጠናና ገንዘብ እንደተሰጣቸውም ተገልጿል። ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች እንዲከላከሉ ውሳኔ አስተላልፏል።


No comments:

Post a Comment