Tuesday, October 28, 2014

አቡነ ማትያስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለን አካል አክራሪና አሸባሪ ካሉ በውግዘት እንደሚለዩ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው! የዕለቱ የምልአተ ጉባኤው ውሎ በድንገት ተቋረጠ

ያደረውን የሕገ ቤተ ክርስቲያን አጀንዳ በፈቃዳቸው ትተው ሌላ ርእሰ ጉዳይ አንሥተዋልየተቃወሟቸውን አባቶች በአሳፋሪ ንግግሮች በመዝለፍ ለማሸማቀቅ ሙከራ አድርገዋልየሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አጀንዳ ቀጣይነት በድምፅ ሊወሰንበት እንደሚችል ተመልክቷልእንደ ሕጉ ስብሰባውን በአግባቡ ካልመሩ ምልአተ ጉባኤው ሌላ ሰብሳቢ መርጦ ይቀጥላል
‹‹ተጠሪነትዎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ሕግ ቢመሩ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን ቢያከብሩ ይሻልዎታል፤ ሕግ አይገዛኝም ካሉ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንሔዳለን፡፡›› /ቅዱስ ሲኖዶሱ/በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነው በተፃራሪ ማኅበሩ ለልዩ ጽ/ቤታቸው ሳያሳውቅ አንዳችም መርሐ ግብር እንዳያከናውንናከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ የሚወስዷቸውን ሕገ ወጥ ርምጃዎች መከላከልን በተመለከተ መመሪያ እንዲሰጥ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው እና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠይቀዋል፡፡‹‹ማኅበራት ገንዘባቸውን ወደ ማእከላዊ ካዝና ያስገቡ ይላሉ፤ የማኅበራት ዓላማ ገንዘብ ማሰባሰብ አይደለም፤ ገንዘብ አሰባሳቢ አይደሉም፤ ለተቋቋሙበት ዓላማ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ግን እንዴት ሥራ ላይ እንዳዋሉት መቆጣጠር ይገባል፡፡››‹‹ዓላማዎ ማኅበሩን መዝጋት ነው፤ አይደለም? አይዘጋም!››

/የምልአተ ጉባኤው አባላት/

* *

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አክራሪና አሸባሪ ሊባል የሚችልና የሚገባው አካል እንደሌለ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላት ገለጹ፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም በማንኛውም መድረክ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለን አካል/ተቋም አክራሪና አሸባሪ ከማለት እንዲቆጠቡ ምልአተ ጉባኤው በጥብቅ አስጠንቅቋቸዋል፡፡

‹‹በቤታችን ውስጥ አክራሪና አሸባሪ የሚባል አንድም አካል የለንም፤›› ያሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ፓትርያርኩ ሌሎች በሌላ መድረክ እንደሚሉት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለን አካል አክራሪና አሸባሪ የሚሉ ከኾነ ‹‹ተወጋግዘን እንለያያለን›› ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋቸዋል፡፡

ፓትርያርኩ በምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው፣ ቤተ ክርስቲያን በአክራሪነት የምትፈረጀው፣ ‹‹ማኅበራት በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት ስለሚሰበስቡ ነው፤›› በማለት ‹‹በሕግ ማስተካከል አለብን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚኽም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ‹‹ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሔ አስቀምጣለኹ›› በሚል ለውይይት በቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ÷ ማኅበራት ገንዘባቸውን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድና ተጠሪነታቸውም ለቅ/ሲኖዶሱ መኾኑ ቀርቶ ለፓትርያርኩ እንዲኾን የሚደነግግ አንቀጽ ካልገባ በሚል የምልአተ ጉባኤውን ሒደት ለተከታታይ ኹለተኛ ቀን እግዳት ውስጥ ከተውት ውለዋል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የማሻሻያ ረቂቅ የማኅበራትን ጉዳይ ጨምሮ በፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ጎልተው የወጡ ሦስት ዐበይት ነጥቦችን ባስቀመጠው ልዩነት ትላንት የተጀመረው ፍጥጫ የተሞላበት ውይይት በዛሬ፣ ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የቀትር በኋላ ውሎው ወደለየለት መካረር አምርቶ ብዙም ሳይቆይ ለስብሰባው በድንገት መቋረጥ ምክንያት ኾኗል፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፣ ጠዋት ስብሰባው እንደተጀመረ ርእሰ መንበሩ ከትላንት ለዛሬ ስላደረው አጀንዳ ምንም ሳያሳውቁ በቀጥታ በደቡብ አፍሪቃ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ስላለው አለመግባባት ወደተመለከተው አጀንዳ አለፉ፡፡ በአንዳንድ የስብሰባው ምንጮች መረጃ፣ ፓትርያርኩ ለአኹኑ እንተወው በሚል ወደ ግንቦት እንዲሸጋገር ጠይቀው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ኹኔታው ለጊዜው በዝምታ ቢታለፍም በሻይ ዕረፍት ሰዓት ብፁዓን አባቶች በጉዳዩ ላይ ተነጋግረውበት ከዕረፍት መልስ የአርቃቂው ኮሚቴ አባል በኾኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥያቄ ተነሥቷል፡፡

‹‹ለምን ወደ ሌላ አጀንዳ ይገባል፤ ጉዳዩ በዚኽ መልክ መታለፉ አግባብ አይደለም፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው የልዩነት አቋም የተያዘባቸው የአጀንዳው ነጥቦች በውይይት እልባት እንዲያገኙ አልያም ምልአተ ጉባኤው በሕጉ መሠረት ድምፅ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

ፓትርያርኩም የትላንቱን አቋማቸውን እየመላለሱ ‹‹ገንዘባቸውን ገቢ ያደርጋሉ፤ ገቢ ካላደረጉ በተኣምር አጀንዳውን አናየውም፤ ወደ ሌላው ጉዳይ እንግባ፤›› ይላሉ፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ‹‹ማኅበራት በበጎ ፈቃድ ለተነሡበት አንድ ዓላማ የቆሙ እንጂ ገንዘብ አሰባሳቢ አይደሉም፤ ለተቋቋሙበት ዓላማ ለመሥራት ያሰባሰቡትን ገንዘብ ግን እንዴትና ምን እንደሠሩበት መቆጣጠር ይገባል፤›› በሚል አቋማቸው ያለበትን ግድፈት እየነቀሱ የቀናውን ለማመላከት ይሞክራሉ፡፡ በትላንት ውሏቸው እንዳደረጉትም ፓትርያርኩ ‹‹ማኅበራት›› ሲሉ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን እንደተናገሩ በመውሰድ የማኅበሩ አጀንዳ በወቅቱና በተራው እንዲታይ ያማፅኗቸዋል፤ ነገር ግን መግባባት ባለመቻሉና የምሳው ዕረፍት በመድረሱ ጉባኤው ይነሣል፡፡


No comments:

Post a Comment