Thursday, October 16, 2014

በጋምቤላ ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ነው

የአካባቢው ምንጮች አቦቦ በሚባለው አካባቢ የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ ወታደሮች የሚወስዱትን እርምጃ በመቃወም መንግስት ያስታጠቃቸው ከ15 በላይ ታጣቂዎች ስርአቱን አናገለግልም በማለት መጥፋታቸውንና የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ታጣቂዎችን ለመያዝ አሰሳ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የመንግስት ታጣቂዎች የነበሩ የጋምቤላ ተወላጆች ከመጥፋታቸው በፊት በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በመወሰዱት እርምጃ ከ2 ያላነሱ የመከላከያ አባላት መገደላቸውና የተወሰኑትም መቁሰላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

በመዠንገር አካባቢ የተነሳውን ግጭት ለመቆጣጠር መንግስት አሁንም የመከላከያ ሃይሉን በስፋት አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ በመዠንገር ተወላጆች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊትን ዋቢ በማድረግ ወኪላችን ገልጿል። በርካታ ቁጥር ያላቸው የመዠንገር ተወላጆችና የወረዳ አመራሮች መታሰራቸውን የገለጸው ወኪላችን፣ የታሰሩት ተወላጆች የቶር መሳሪያ እንዳልተገኘባቸው አክሎ ተናግሯል።

በሌላ በኩል ከ40 ያላነሱ የፌደራል ፖሊሶችና ከ10 በላይ የመከላከያና የወረዳ ታጣቂዎች የተገደሉበትን ግጭት በተመለከተ መረጃ ያካፈሉን የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከ30 በላይ የሚሆኑ የፌደራል ፖሊሶች የተገደሉት በኦራል መኪና ላይ እንዳሉ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ነው። ጥቃቱን ተከትሎ ታጣቂዎቹ መሳሪያዎችና ከርቀት ማሳያ መነጽሮችን መውሰዳቸውን ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።

በጋምቤላ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት የነበረው ውጥረት እየቀነሰ በመምጣጡ ሱቆች መከፈት መጀመራቸውንና የከተማው ህዝብ ከቤት መውጣት መጀመሩን የሚገልጹት ነዋሪዎች ሁኔታው ግን አሁንም አስፈሪ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በአካባቢው ለሚታየው ግጭት አንዳንድ የአካባቢው ባለስልጣናትንና ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ ቢያደርጉም ስለተገደሉት የፌደራል ፖሊሶችና የመከላከያ አባላት ሰይናገሩ ቀርተዋል። አቶ ግርማ ሰይፉም ጉዳዩን በተመለከተ ለጠ/ሚንስትሩም ጥያቄ አላቀረቡም።


No comments:

Post a Comment