Tuesday, September 13, 2016

የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰደ ያለው ከመጠን ያለፈ ዕርምጃ እንዳሳሰበው ገለጸ

ኢሳት (መስከረም 3 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግስት ህጻናትን ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ አመራሮችና ሰላማዊ ሰፈኞች ላይ እየወሰደ ያለው ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ አሳስቦት እንደሚገኝ ማክሰኞች በድጋሚ ገለጠ።
በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ በብሪታኒያ የተሰባሰቡ የኮሚሽኑ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የጅምላ እስራት እያካሄዱ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 
የኮሚሽኑ ሃላፊ የሆኑት ዘይድ ራድ አል ሁሴን በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የጅምላ እስራትና የሰዎች ደብዛ መጥፋት እንዲሁም የህጻናት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ለአለም አቀፍ አካላትና በመድረኩ ለተሳተፉ የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታውቀዋል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሃገሪቱ በመፈጸም ላይ ያሉ ግድያዎችን በገለልተኛ ቡድን እንዲጣራ ጥያቄን ቢያቀርብም የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ድረስ ምላሽ ነፍጎ መገኘቱን ሃላፊው ለአለም አቀፍ ተቋማት ማስረዳታቸው ታውቋል። 

በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀውን ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች መሞታቸውን ያወሱት የኮሚሽኑ ሃላፊ፣ መንግስት ሰላማዊ ጥያቄን በሚያነሱ አካላት ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህ አለም አቀፍ መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበረውና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን የሚከታተለው ሪፕሪቭ የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ኮሚሽኑ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ የተወሰደውን ድርጊትና የእስር ሁኔታ በመድረኩ መንቀፉን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ያቀረበውን የምርመራ ጥያቄ ተከትሎ መቀመጫቸውን በተለያዩ የአለማችን ሃገራት ያደረጉ 14 አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኮሚሽኑ ተጨማሪ እርምጃን እንዲወስድ ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሃገር በቀል አካላት ማጣራት ይካሄድበታል ቢሉም ማጣራቱ መቼ እንደሚጀመርና በማን አካል እንደሚከናወን የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
ይኸው ለወራት በኦሮሚይ ክልል የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ድረስ በተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።

No comments:

Post a Comment