Thursday, September 29, 2016

በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) የሚከበረውን የእሬቻ በዓልን አስመልክቶ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት መሰማራቱ ተገለጸ

ኢሳት (መስከረም 19 ፥ 2008)

የፊታችን ዕሁድ በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ ለሚከበረው አመታዊው የእሬቻ በዓል አከባባር በሚል ቁጥር ከፍተኛ የሆነ የፌዴራል የክልል የጸጥታ ሃሎች በከተማዋ መሰማራታቸውን እማኞች ለኢሳት ገለጹ።
የበዓሉ አከባበር ዝግጅትን ተከትሎ ወደ ከተማ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ በመደረግ ላይ መሆኑም ታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ከወራት በፊት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ ዙሪያዋ ባሉ የገጠር ወረዳዎች ህዝባዊ ትዕይንቶች ሲካሄዱ የንበረ ሲሆን፣ በእሬቻ በዓል አከባበር ወቅትም ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ባለመኖሩ የጸጥታ ቁጥጥር በመደረግ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

የበዓሉ አስተባብሪዎች በበኩላቸው በደማቅ ሁኔታ የፊታችን እሁድ ለሚከበረው የእሬቻ በዓል ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውና በክልሉ ለወራት ዘልቆ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ቢሾፍቱ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በክልሉ ከዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ ከ500 የሚገልጡ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ይገልጻሉ።
ይሁንና ተቃውሞው ወደ አማራ ክልል ጭምር በመዛመቱ ድርጊቱ ለመንግስት የጸጥታ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።
በተያዘው ሳምንት በመላው ሃገሪቱ ከተከበረው የደመራ በዓል ዝግጅት ጋር በተገኛኘ በኦሮሞያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ስር በምትገኘው የጊንጪ ከተማ ተቃውሞ መካሄዱን ይታወሳል።
በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ እንዲሁ በበዓሉ ዋዜማ አንድ ታዳጊ ወጣት በፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች ግድያ እንደተፈጸመበት እማኞች ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

No comments:

Post a Comment