Thursday, September 15, 2016

የመንግስት ሃይሎች በሰገን ልዩ ዞን ጎማይዴ ወረዳ የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆችን ከመኖሪያ ከቀያቸው እያፈናቀሉ ነው ተባለ

ኢሳት (መስከረም 5 ፥ 2009)
በደቡብ ክልል ስር በሚገኘው የሰገን ልዩ ዞን ጎማይዴ ወረዳ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በአካባቢው ለዘመናት በኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ከቀያቸው የማፈናቀል እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን እማኞች ሃሙስ ለኢሳት አስታውቁ። 
ሰሞኑን የጸጥታ ህያሎች የመኖሪያ ቤቶች እንዲቃጠሉ ያደረጉትን ድርጊት ተከትሎ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ገልጸዋል። 
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በዞኑ ስር የሚገኙት የኮንሶ ብሄረሰብ ያነሱትን አስተዳደራዊ ጥያቄ ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማዞር ሆን ብለው የወሰዱት እርምጃ ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። 

ድርጊቱ የእርስ በዕርስ ግጭትን ለመቀስቀስና ሃሳብን ለማስቀየር ያለመ ነው ሲሉ የገለጹት እማኞች በተቃራኒው የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ምግብ በማቅረብና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አንድ መሆናቸውን እያሳዩ እንደሚገኝ ከዜና ክፍላችን ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ እማኞች አስረድተዋል።
የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ በልዩ ዞን ወረዳ አልያም በዞን ስር እንዲተዳደሩ ጥያቄን ቢያቀርቡም የደቡብ ክልል መንግስት ጥያቄን ቢያቀርቡም የደቡብ ክልል መንግስት ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ ይታወሳል።
ይሁንና የብሄረሰቡ አባላት አሁንም ድረስ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ጥረትን ቢያደርጉም ጥያቄው ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲያመራ የክልሉ መንግስትና የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች የኢሰብዓዊ ድርጊትን እየፈጸሙ እንደሆነ የአከኣባቢው ነዋሪዎች አክለው አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በዞኑ አለመረጋጋትና በመንግስትና በአካባቢው ነዋሪዎችን ዘንድ አለመተማመን መኖሩን እማኞች አክለው አስታውቀዋል።
በዞኑ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት የሰጡት ምላሽ የለም።

No comments:

Post a Comment