Thursday, September 15, 2016

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ አገራት ወደአለመረጋጋትና ሁከት ሊገቡ እንደሚችሉ አሜሪካ አሳሰበች

ኢሳት (መስከረም 5 ፥ 2009)
የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ የአለማችን ሃገራት ለችግሩ ዕልባትን የማይሰጡ ከሆነ ወደ ዘላቂ አለመረጋጋትና ሁከት ሊገቡ እንደሚችሉ አሜሪካ ሃሙስ አሳሰበች። 
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት በስላማዊ ሰልፎች ላይ ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ እንደተጠቀመ የገለጸችው ሃገሪቱ ጭቋኝና አፋኝ የሆኑ ሃገራት ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ከዜጎቻቸው ጠንካራ ተቃውሞ እየቀረበባቸው መሆኑን አስታወቀች። 
ሃሙስ በአለም ዙሪያ የተከበረውን የአለም አቀፉን የዴሞክራሲ ቀን አስመልክቶ መግለጫን ያወጣው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነጻነትና ዴሞክራሲ የአንድን ሀገር ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው አመልክቷል። 
በሃገራቸው መንግስታት ጭቆና እየደረሰባቸው የሚገኙ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች በአሁኑ ወቅት በርካታ አማራጮችን በመጠቀም የሃገራቸው መንግስትን ግልፅና ተጠያቂ ለማድረግ እርምጃን እየወሰዱ ይገኛል ሲል የአሜሪካን መንግስት ገልጿል። 
መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸሙ ያሉ ሃገራት እየቀረቡ ላሉ ሰላማዊ ትግሎች ምላሽን የማይትሰጡ ከሆነ ድርጊቱን ለመቆጣጠር ሳይሆን አለመረጋጋትና ሁከት ሊከተል እንደሚችል መልዕክታችንን ማስተላለፍ እንወዳለን ሲል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመልዕክቱ አስፍሯል።
በኢትዮጵያ ለወራት የዘለቀን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ አሜሪካ የኢትዮጵያው መንግስት ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃ ተጠቅሟል ስትል ቅሬታ ማቅረቧ ይታወሳል።
ሃገሪቱ ይፋ ያደረገችውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተፈጽሟል የተባሉ ግድያዎችንና የጅምላ እስራቶችን በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄደበት በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን የሃይል እርምጃ በማቆም ጥያቄን እያቀረቡ ካሉ አካላት ጋር ምክክርን እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ለቀረበው ጥያቄ ተባባሪ እንደማይሆን ምላሽን የሰጠ ሲሆን፣ የደረሱ ጉዳዮችን በሃገር በቀል ተቋማት ማጣራ ይካሄድበታል በማለት ምላሽን ሰጥቷል።
ይሁንና ማጣራቱ በማንና መቼ እንደሚካሄድ የተገለጸ ነገር የለም። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በበኩላቸው መንግስት አካሂደዋለሁ የሚለው ምርመራ ተዓማኒነት እንደማይኖረው በመግለጽ ላይ ናቸው።

No comments:

Post a Comment