Friday, September 30, 2016

በቤኒሻንጉል ጊዛን ወደ 300 የሚጠጉ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ጫካ መግባታቸው ተነገረ

ኢሳት (መስከረም 20 ፥ 2009)
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጊዛን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ግጭት እልባት አለማግኘቱን ተከትሎ ወደ 300 የሚጠጉ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ጫካ መግባታቸውን እማኞች አርብ ለኢሳት ገለጡ። 
በነዋሪዎችና ከትግራይ ክልል መጥተው ሰፍረዋል በተባሉ 1ሺ አካባቢ ሰዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት በትንሹ ስምንት ከሚሆኑ የመንግስት የጸጥታ አባላት ግድያ ምክንያት መሆኑን ሃሙስ መዘገባችን ይታወሳል። 
ድርጊቱ እልባት ሳያገኝ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉን የተናገሩት የሸርቆሌ ከተማ አካባቢ ነዋሪዎች ግጭቱን ተከትሎ ወደ 300 የሚጠጉ ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ወደ ጫካ መሰደዳቸውን አስረድተዋል። 

የቤኒሻንጉል ህዝብ ንቅናቄ አመራሮችና የጊዛን ሸርቆሌ አካባቢ ነዋሪዎች በቅርቡ ከትግራይ ክልል የመጡ 1ሺ አካባቢ ሰዎች ለወርቅ ልማት በሚል በመከላከያ አዛዦች በስፍራው መሰማራታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
የክልሉ መንግስትና የሸርቆሌ ወረዳ አስተዳደሪዎች ሰፍረው የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ፍላጎት ቢኖራቸውም ሰፋሪዎቹ የመንግስት ወታደራዊ ሃይሎች ድጋፍን መከታ በማድረግ ለቀረበላቸው ጥያቄ ተባባሪ አለመሆናቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ወደ ጫካ ከተሰደዱት ሰዎች መካከልም ለወርቅ ልማቱ የሰፈሩትና ነባር ነዋሪዎች እንደሚገኙበት ከዜና ክፍላችን ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት እማኞች አክለው ገልጸዋል።
ረቡዕ በተቀሰቀሰው የሁለቱ ወገኖች ግጭት ከተገደሉት ስምንት የጸጥታ አባላት በተጨማሪ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር የቤኒሻንጉል ህዝብ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ ሃሚድ ናስር አስረድተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መጠነ ሰፊ የሆነ የወርቅ ሃብት ክምችት እንዳለው አንድ የግብፅ ኩባንያ ከሁለት አመት በፊት ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment