Thursday, September 29, 2016

በቃሊቲ በሚገኙ እስረኞች ላይ የሚደረገው ጫና መቀጠሉ ተነገረ

ኢሳት (መስከረም 19 ፥ 2008)

በቃሊቲ ወህኒ ቤት በሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚፈደረገው ጫና እና ማሰቃየት መቀጠሉ ታወቀ። የ18 ዓመታት እስራት ተፈርዶበት ላለፉት 5 አመታት በዚህ ወህኒ ቤት በሚገኘው በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ በእስር ቤቱ ሃላፊዎች የሚፈጸመው ጥቃት መቀጠሉን እንዲሁም የማበሳጨት ዕርምጃዎች መጨመራቸውን መረዳት ተችሏል።
በቅድሚያ የጻፋቸውን ማስታወሻዎች፣ በኋላም ማናቸውንም የጽህፈት መሳሪያና ባዶ ወረቀቶች ጭምር የነጠቁት የእስር ቤቱ አዛዦች የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዳወደሙበትም በቅርቡ ከእስር ቤት የወጣ ግለሰብ ለኢሳት አብራርቷል።

በዚህ እስረኛ ገለጻ መሰረት ሰሞኑን ፍተሻ በሚል ብርበራ ያካሄዱት የእስር ቤቱ ሃላፊዎች እስክንድር ልብስ የሚያስቀምጥበት ሻንጣ ሲወሰዱ፣ ልብሱን ሜዳ ላይ እንደበተኑት የገለጸ ሲሆን፣ ሻንጣውን ሲወስዱ የሰጡም ምክንያት አልነበረም። እስረኛው እስሩን ጨርሶ እስከወጣበት  ዕለት ድረስ ሻንጣዎም ሆነ ሌሎች ንብረቶች እንዳልተመለሰለት ገልጿል።
ከአንድነት አመራሮች አንዷለም አራጌና ናትናዔል መኮንን ጋር መስከረም 3 ቀን 2004 ዓም የታሰረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለፉት 5 አመታት በወህኒ ቤት የቆየ ሲሆን፣ የ18 ዓመታት እስራት እንደተፈረደበትም ይታወሳል።
ከፔን አሜሪካና ሂውማን ራይትስ ዎች ከመሳሰሉ የሰብዓዊና የጸሃፊያን ድርጅቶች አለም አቀፍ ሽልማት የተቀበለው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ሃሳቡን በነጻነት በመግለጹ ሳቢያ መታሰሩን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጆን ኬሪ ምስክርነት መስጠታቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment