Thursday, September 29, 2016

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተቀሰቀሰ ግጭት 8 የጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ

ኢሳት (መስከረም 19 ፥ 2008)

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሰርቀሌ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በነዋሪዎችና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ 8 የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን እማኞች ለኢሳት ገለጹ።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉት በስፍራው ወርቅ ለማውጣት በሚል በቅርቡ ከ1ሺ በላይ የትግራይ ተወላጆች መስፈራቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አለመግባባት መሆኑ ተነግሯል። በዚሁ ግጭት ከተገደሉት የጸጥታ ሃይሎች በተጨማሪ ከ20-30 የሚደርሱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የቤኒሻንጉል ህዝብ ንቅናቄ አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ ሃሚድ ናስር በቅርቡ በአካባቢው ያለን የወርቅ ሃብት ለማልማት በሚል ከትግራይ ክልል የመጡ ወታደራዊ አመራሮችና ሌሎች አካላት በጊዛን ሸርቆሌ መስፈራቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
በአካባቢው ተካሄዷል ያሉትን ህገወጥ ወራራ ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱንና ሰፋሪዎችም ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ረቡዕ ግጭት መቀስቀሱን ገልጸዋል።
በነዋሪዎችና የወርቅ ሃብት ያለበትን ይዘው በሚገኙ አካላት ዘንድ በተፈጠረው ግጭት በትንሹ ስምንት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውንና አካባቢው በውጥረት ውስጥ መሆኑን የንቅናቄው ሃላፊ አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment