Tuesday, September 13, 2016

በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለም አቀፍ ትኩረት እያገኘ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (መስከረም 3 ፥ 2009)
ባለፉት በርካታ ወራት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአሜሪካ መንግስት ምክር ቤት ትኩረት እያገኘ እንደሆነ አንድ የአሜሪካ ኮንግረስ ምክር ቤት ተወካይ ተናገሩ። 
የኮሎራዶ ሴናተር የሆኑት ኮንግሬስ ማን ማይክ ኮፍማን ለኢሳት በሰጡት ቃለ-ምልልስ፣ ኢትዮ-አሜሪካውያን በየግዛታቸው ለሚገኙ የኮንግሬስ ለወኪሎቻቸው በመደወል የኢትዮጵያ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርበዋል። 
አሜሪካ አሁን ያላትን አለም-አቀፋዊ ተሰሚነት ተጠቅማ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ሰብዓዊ መብት እንዲያከብር ተፅዕኖ እንድታሳርፍ ኮንግሬስማን ማይክ ኮፍማን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካ መንግስት የቀረበውን የመፍትሄ ሃሳብና፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን የገለልተኛ አጣሪ ቡድን የቀረበውን ሃሳብ ካላከበረ፣ የአሜሪካ ኮንግሬስ ሌላ መፍትሄ መፈለግ አለበት በማለት ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ሚስተር ማይክ ኮፍማን ጠይቀዋል።
“አሜሪካ የምትሰጠው የውጭ እርዳታ መከለስ ሊኖርብን ነው” ያሉት ኮንግሬስ ማን ማይክ ኮፍማን፣ ሰላማዊ ህዝብን ለማሸበር የሚውል የአሜሪካ እርዳታ መመርመር ይኖርበታል ሲሉም አስታውቀዋል።
“አቅማችንን ተጠቅመን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ መቻል አለብን” በማለት አክለው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀረበውን የገለልተኛ አጣሪ ቡድን ጥሪም አሜሪካ ድጋፍ እንድታደርግ ኮንግሬስ ማን ማይክ ኮፍማን ጠይቀዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አቶ ግርማ ብሩንም በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያና የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ባለው የሃይል እርምጃዎች እንዲያቆመው መጠየቃቸውንም ኮሎራዶ ግዛት የአሜሪካ ኮንግሬስ ተወካይ የሆኑት ሚስተር ኮፍማን ለኢሳት ተናግረዋል።
“አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ መንግስት የሚያስበው አይነት አይደለም” ያሉት ኮንግሬስማን ማይክ ኮፍማን፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም አሳታፊ መንግስት መምጣቱ አይቀርም” በማለት ለወደፊት የኢትዮጵያ መንግስት የሁሉንም ሃሳብና ፍላጎት ያንጸባረቅ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ባለፈው ሚያዚያ የሜሪላንድ ግዛት ሴናተር ቤን ካርዲን፣ እንዲሁም ሴናተር ሩቢዮ ሌሎች 9 ሴናተሮች ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ህወሃት/ኢህአዴግ ፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ የአሜርካ መንግስት እንዲያጣራ ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስትም በተዋዋሚዎች፣ ጋዜጠኞችና፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆም ሴናተሮቹ ሲጠይቁ፣ በግፍ የተገደሉ ሰዎችን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን እንዲያቋቁምና፣ የአለመረጋጋት መንስዔ የሆኑትን የአገዛዙና ሌሎች ቡድኖችና ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲደረጉ መምከራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ኢትዮጵያን የሚመለከተው የመፍትሄ ሃሳብ ዛሬ ማክሰኞ ሴፕቴምበር 13 ፥ 2013 ይቀርባል ተብሏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት፣ ዴሞክራሲና፣ ፍትህ ላይ የሚሰራው የኢትዮጵያ አድቦኬሲ ኔትዎርክ አመራር አባል የሆኑን አቶ ነዓምን ዘለቀ እና የኮሎራዶ የአድቦኬሲ ኔትዎርክ አስተባባሪ አቶ ዮፍታሄ ሃይሉ ከኮንግረስ ማይክ ኮፍማን ጋር በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የዴሞክራሲ እጦትና፣ የዜጎች ፍትህና ነጻነት ማጣት ትኩረት ተሰጥቶባቸው ውይይይት ተደርጎባቸዋል።

No comments:

Post a Comment