Friday, September 30, 2016

በቢሾፍቱ ከተማ ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

ኢሳት (መስከረም 20 ፥ 2009)
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከነገ በስቲያ እሁድ በበሾፍቱ ከተማ ለሚከበረው የእሬቻ በዓል ልዩ ሃይል ተመድቦ የጸጥታ ቁጥጥር በመደረግ ላይ መሆኑን አርብ አስታወቀ። 
የከተማዋ ነዋሪዎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ በመሰማራት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ፍተሻ በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ረቡዕ ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል። 
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አርብ ባወጣው መግለጫ በከተማ የበዓሉ አከባበር በሰላም እንዲስተናገድ ለማድረግ ታስቦ ልዩ ሃይል መመደቡንና ከነዋሪዎች ጋር በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር መካሄዱን አመልክቷል። 

በኦሮሚያ ክልል በበርካታ ከተሞች ለወራት ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ በደብረ ዘይትና ዙሪያዋ ባሉ የገጠር ከተሞች ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞ በበዓሉ አከባበር ወቅት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ጥበቃው ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከሩን ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባና አዳማ ናዝሬት በኩል ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ፍተሻ እየተካሄደባቸው መሆኑን የተናገሩት እማኞች የበዓሉ ዝግጅት ከአከባበሩ በላይ አለመረጋጋት መስፈኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ህብረተሰቡ የጸጥታ ስጋት የሆኑ ነገሮችን ሲመለከት ለጸጥታ ሃይል መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል። የበዓሉ አስተባባሪዎች ወደ 3ሺ የሚተጋ ሰው በእሬቻ አመታዊ በዓል አከባባር ላይ በመታደም ወደ ቢሾፍቱ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment