Thursday, September 15, 2016

በጎንደር ትጥቅ ለማስፈታት የተደረገው ሙከራ ግጭት ቀሰቀሰ

ኢሳት (መስከረም 5 ፥ 2009)
በሰሜን ጎንደር ዞን ስር በሚገኙት የአምባ ጊዮርጊስና በለሳ አርባይ ከተሞች ነዋሪዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተሞከረው እንቅስቃሴ ግጭት መቀስቀሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ሃሙስ ለኢሳት ገለጹ። 
ከረቡዕ ጀምሮ በከተሞቹ የተቀሰቀስው ግጭት ዕልባት አለማግኘቱን የተናገሩት ነዋሪዎች ሃሙስ ለሁለተኛ ቀን ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ ማምሸቱን እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል። 

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቅርቡ በክልሉ የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በማድረግ በአካባቢው የታጠቁ ነዋሪዎችን መሳሪያ ለማስፈታት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆናቸው ታውቋል። 
ይሁንና በክልሉና በፌዴራል የጸጥታ አባላት እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ በሁለቱ ከተሞች ያልተጠበቀ ተቃውሞ እንዳጋጠመውና በአካባቢው ውጥረት መንገሱን ለደህነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግልጽ ያልፈለጉ እማኝች ለኢሳት ተናግረዋል።
በሁለቱ ከተሞች ያለው ውጥረት የተረጋጋ ባለመሆኑ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለ ነዋሪዎች አክለው አሰረድተዋል።
ይሁንና መሳሪያን ላለመስጠት የወሰኑ ነዋሪዎች በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ያስረዱት እማኞች ነዋሪዎች መረጃዎችን በመለዋወጥ የአጸፋ እርምጃን እየወሰዱ እንደሚገኝ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አክለው ገልጸዋል።
ከሃምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙ የጎንደርና የባህር ዳር ከተሞች እንዲሁም በአጎራባች የዞን አካባቢዎች ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ መሰንበቱ ይታወሳል።
የመንግስት የጸጥታ ህያሎች ተቃውሞን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃ በጎንደርና ባሀርዳር ከተሞች በቻ ከ 50 በላይ ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልጹ ቆይተዋል።
በክልሉ ያለው ተቃውሞ እልባት አለማግኘቱን የተናገሩት እማኞች በተለያዩ ከተሞች ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ እንደሚገኝ አክለው አስረድተዋል።

No comments:

Post a Comment