Thursday, May 14, 2015

ፕሮፍ. መስፍን ወልደማርያም፡- አማራ የሌለው የት ሄዶ ነው?

ከመለክ ሐራ

እኔ ልናገረዎ የማይገባ ብላቴና ነኝ፡፡ በብዙ ነገር አድናቂዎ እና ብዙዎችን ጽሁፎችዎን ያነበብኩ ነኝ፡፡ አሁን ለያዝኩት ማንነትም የእርስዎ አስተዋጽኦ አለበት፡፡ ይሁንና በአማራ ጉዳይ ላይ ባለዎት አቋም ላይ ከረር ያለ ልዩነት አለኝ፡፡ ሰው መሆን አቅቶኝ እና የጎሰኝነት ስሜት አጥቅቶኝ ሳይሆን ይህ የለም እየተባለ መከራ የሚወርድበት ህዝብ ረፍት ስላጣና ዜግነቱን ስለተነጠቀ እንዲሁም አለሁልህ የሚለው ስላጣ አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ልሟገትለት ራሴን ስላዘጋጀሁ እርስዎንም አሻቅቤ ለመናገር ተገድጃለሁ፡፡ ስለራሴ ስል የእርስዎ እምነትና ፍልስፍና ነው ያለኝ፡፡ ስለህዝቤ ስል ግን ከዚህ ሸሽቻለሁ፡፡ እንዳይቀየሙኝ፡፡

የክህደት ቁልቁልት በተባለው መጽሀፍዎ ምእራፍ 11 ላይ ያተቱት የአማራ አለመኖር

አማራ ማለት ሀይማኖት ነው ስላሉ በአለም ላይ ያሉ ትናንሽና ትላልቅ እምነቶች ውስጥ ዝርዝሩን ለማግኘት ብዙ ደክሜ ሳላገኘው ቀረሁ፡፡ አማራ ማለት ክርስቲያን ከሆነ አገው ለምን አማራ እንዳልተባለ እንዲያብራሩልኝ እጠይቃለሁ፡፡ ሁለቱም ቅዱስ ላሊበላ የምትሄዱ አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ እያሉ ለዘመናት በአንድ የክርስትና ማእድ ሲሳተፉ ኖረዋል፡፡ አንዱ አገው አንዱ አማራ ሆነው፡፡ አማራው ታዲያ ለምን ሁለት የክርስትና ስም አስፈለገው–አማራ እና ክርስቲያን የሚል? ከተለያዩ ጸሀፍት እንደጠቃቀሱትም አማራ ማለት ነጻ የወጣ ህዝብ (ከአረማዊነት የተመለሰ) ማለት ነው፡፡ ታዲያ አገው ነጻ አልወጣም ማለት ነው? ትግሬ ነጻ አልወጣም ማለት ነው? ወይስ የተለያየ አይነት ክርስትና ነው ያለው–አንዱን ነጻ የሚያወጣ ሌውን ነጻ የማያወጣ? እንደገና በአማራ መሀል የሚኖሩት አርጎባዎች እስላም ናቸው፡፡ ከሌላው እስላም ተለይተው ለምንድን አርጎባ የሚል ስም የያዙት? እነሱ የአርጎባ ጎሳ እስላሞች ሲሆኑ ከአርጎባ ውጭ ያለው ምን ሊሆን ነው?


የጠቀሷቸው ጸሀፍት ወደሀይማኖታቸው የሚያደሉ እንጅ ቁሳዊ ምሁራን እንዳልሆኑ እርስዎ ያውቃሉ፡፡ ከዛም የተነሳ ለእምነታቸው ያደላሉ፡፡ አማራ የሚለውንም የእምነታቸው ዘብ አደረጉት፡፡ ይሁንና አማራ ነጻ ህዝብ የሚለው ራሱ ከጠቀሷቸው ጽሁፎች መረዳት እንደሚቻለው ሀይማኖታዊ ይዘት ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ሁለት አንድምታ ነው ያለው፡፡ ወደክርስትና የገባ እና ጦረኛ ሆኖ በነጻነት የሚኖር የሚል፡፡ እርስዎ ግን ጦረኛነቱን ሊያተኩሩበት አልፈለጉም፡፡ ለምን ቢባል ጦረኛነት ክርስትና ከሚለው ትርክትዎ ሊየስወጣዎ ስለሚችል፡፡ እንደሚታወቀው ሰው ወደክርስትና ሲገባ የጎሳ ጦረኝነቱ ይቀንሳል፡፡ እርስዎ የጠቀሷቸው ምንጮች የሚሉት ግን ጦረኛ የሆነና ራሱን ከሌላ ጎሳ ይሁን ከምንም ነገር አስከብሮ የሚኖር ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄው ታዲያ ይህ ህዝብ እርስዎ እንደጠቀሱት ከየነገዱ ጦረኛው ተሰብስቦ አማራ ተባለ ወይስ መጀመሪያውንም አማራ የተባለ ጦረኛ ነገድ ነበር የሚለው ነው፡፡ የእርስዎን ትርክት ብንቀበል እንኳ ቤተ አምሐራ የሚለው ነገር ያፈርሰዋል፡፡ ለምን ላስቴዎች ናቸው ይህን የተሰባሰበ ህዝብ አምሐራ ያሉት፡፡ እናም ይህንን አምሐራ ላስታ በቤተምንግስታቸው ዙሪያ አሰፈሩት ወይስ ራቅ አድርገው ቤተ አምሐራ የተባለ ቦታ ውስጥ ወስደው አሰፈሩት የሚለውን ጥያቄ በግድ መመለስ አለብዎት፡፡ ለምን ቢሉ ሁለቱ የሰማይና የምድር ያህል የሚራራቁ ተቃራኒ አስተሳሰቦች ስለሆኑ፡፡

ከአለቃ አስሜ የጠቀሱት “ያልተማረ ጨካኝ ጭፍራ” የሚለው አረፍተ ነገር መላ አማራን ክርስቲያን የማድረግ ክርክርዎን አፈር የሚያበላ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ክርስቲያን ሆነ ማለት ጭካኔው አበቃ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን ሆነ ማለት ተማረ ማለት ነው፡፡ የዛ ጊዜ ትምህርት ሀይማኖትን ከማወቅ የዘለለ ሚና ስለሌለው በተለምዶ ክርስትያን ሆነ ማለት የተማረ ማለት ነው፡፡ የሚማረውም የክርስትና ስነምግባርን ነው፡፡ እርሱም ዋናው ትምህርት የአረማዊ ጸባይ የሆነውን ጭካኔን ማስወገድ ነው፡፡ እና እዚህ ላይ ራስዎን ተዋግተው ወድቀዋል፡፡

አንድ የትግርኛ መዝገበ ቃላት አምሐራ የሚለውን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሎ ቅልብጭ አድርጎ አስቀመጠው ብለዋል፡፡ ይህ ደራሲ ከራሱ ያመነጨውን ሀሳብ ነው የጻፈው ወይስ ከሌላ ምንጭ ያገኘውን ነው ብለው መጠየቅ ነበረብዎት፡፡ ጸሀፊው እንዳለው አማራ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ከሆነ ለምን የትግራይ ሰዎች አማራ አልተባሉም? ወይስ የትግራይ ሰዎች ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለቱ ነው? ቀጥለውም የንቡረ እድን አምሐራ ማለት ከየነገዱ ተሰበስቦ ክርስቲያን የሆነው የእግዚአብሔር ህዝብ እና ፍጹም ሙሉ አንድ አይነት ለሆነው ለኢትዮጵያ ዘር የተሰጠ የሚል የባህታዊ ሀተታ ተቀብለዋል፡፡ እንግዲህ አማራ ማለት የኢትዮጵያ ከእግዜር በጥምቀት የተሰጠ መለኮታዊ ዘር ሀነ ማለት ከባድ ነገር ነው፡፡ አንድ እርስዎ መኖሩን የሚያምኑትን ኦሮሞና ሌላውን ከጨዋታ ውጭ የሚደርግ ነው፡፡ ሲቀጥል ኢትዮጵያዊ ማለት ክርስቲያን ማለት ስለሆነ እስላሞች ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለት ሊሆን ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ ፍጹም አንድ ዘር የሚለው ሙግት ኢትዮጵያዊነት የማይመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ስለፈጠረ እዛው ላይ አፈር በላ ማት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ አምሐራ ማለት ፍጹም ኢትዮጵያዊ ዘር የሚለው ራሱ ስለዘርና ጎሳ ያለዎትን አረዳድ ፈተና ላይ የሚጥል ነው፡፡ በዘርማ ከሄዱ ብዙ ጣጣ ሊመጣ ነው፡፡ የሰው ዘር ሁሉ አንድ ስለሆነ፡፡ ኢትዮጵያዊ ዘር የሚባል ራሱ የለም በዚህ መንገድማ፡፡ የአማራን አለማዊ ህልውና ለመጻፍ ተነስተው ስለሰማያዊ ህልውናው የሚያትቱ ጽሁፎችን ዋቢ ማድረግ በራሱ መልካም አይመስልም፡፡

ማተብ የሚል ሌላ ሃሳብም ተውሰዋል፡፡ ማተብ ማሰር ክርስትና ነው ከተባለ ማተብ ማሰር የተለየ ክስተትን ተከትሎ እንደመጣ መጠርጠር ያሻል፡፡ ከመጀመሪያው የክርስትና ደንብ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ክርስትናና አማራ ከማተብ ጋር ተያይዘው መገለጽ የጀመሩት ከማተቡ ክስተት በፊት ነው ወይስ በኋላ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ ከማተብ በፊት ይህ ህዝብ ማን ይባል ነበር የሚል ሌላ ተቀጣይ ጥያቄ ይወልዳል፡፡ አማራ የለም ብሎ ለመደምደም ይህንን ሁሉ መመለስ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ትልቁ ስህተት አማራ ማለት ሰፊ ነው፤ ማጥበብ አያስፈልግም፤ ጎሳዎች ዝግ ናቸው፤ ማንም ሰው ወደነሱ ገብቶ የነሱን ማንነት ሊያገኝ አይችልም ያሉት ነው፡፡ ይህም ማለት አማራ ጎሳ ስላልሆነ ማንም ቋንቋውን የቻለና ባህሉን የተቀበለ አማራ መሆን ይችላል፡፡ በተጻራሪው ግን ጎሳዎች ዝግ ናቸው ብለዋል፡፡ ይተው እንጅ ፕሮፌሰር፡፡ መቸም ከአይሁድ በላይ ዝግ ነገድ ወይም ጎሳ እንደሌለ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን መጽሀፍ ቅዱስ ወደይሁዲነት የገባ እያለ የሚጠቅሳቸው አይሁዳዊያን ያልሆኑ ህዝቦች የትየለሌ ናቸው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይሆን አማራ በደረሰበት የማህበረሰብ የእድገት ደረጃ ያሉ ነገዶች ወይም ጎሳዎች የእነሱን ባህል ለተቀበለ ሁሉ በራቸው ክፍት መሆኑ ያለና የነበረ ነው፡፡ እዚህ ላይ የአማራ ብቻ ተለይቶ እንደ ተአምር የሚቆጠርበት ምክንያት አይታየኝም፡፡

በምእራፍዎ መጨረሻ ላይ የአማራ ወደጎሳዊ ማንነት መለወጥ የወያኔ ሴራ እንደሆነ፤ አንዳንድ አማሮች እንዳስተጋቡት እና ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ብለው ስጋትዎን አስቀምጠዋል፡፡ ጥሩ፡፡ ጎሰኛነት የአገር አንድነትን ይጎዳል፡፡ ከሰውነት ደረጃ መውረድ እንደሆነም አምናለሁ-አውቃለሁ፤ እቀበላሁ፡፡ ከዚህ ፍልስፍናዎ ጋር አንዳች ልዩነት አይኖረኝም፡፡ ይሁንና ሁሉም ወደየጎሳው ከረጢት ሲከት እያዩት፤ ሁሉም የራሱን የጎሳ ማንነት የሚቀርጸው አማራን ከመጥላት እንደሆነ እያወቁ፤ ኢትዮጵያዊነት በጎሳ ተመንዝሮ የሁሉም ጠላት በተባለ ነገር ግን እርስዎ የለም በሚሉት ጎሳ ላይ ቢላ እየሳለ፤ እያረደም እያዩ፤ ሽንጥዎን ገትረው አማራ የለም ማለትዎ ለማን አተርፍ ብለው ነው? እውን ይህ ህዝብ አውላላ ሜዳ ላይ የማንም ጥቃት ሰለባ መሆኑ እንዴት ሳይታይዎ ቀረ? አማራ ለኢትዮጵያዊነት ሲባል አፈር ደቸ ይብላ የሚል ፍልስፍና የሚያራምዱ ነው የሚመስሉት፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አማራ የሚጠፋባት ኢትዮጵያ ለሌሎች ጎሳዎች አገር እንድትሆን አንጅ ለአማራ እንዳትበጀው ያውቃሉ፡፡ እና ጠፍቶ በጥፋቱ ላይ አገር የሚገነባበት እንዴት ያለ ህዝብ ነው? እና በጠቅላላው በዚህ ጽሁፍዎ አማራን አንዴ ከሀይማኖት፤ ሌላ ጊዜ ከዜግነት፤ አለፍ ሲልም ከጦረኝነት ሲቀጥልም ከኢትዮጵያዊነት ጋር እያምታቱ ጻፉ፡፡

የጠቀሷቸው ጽሁፎች ሁሉ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸውና በይሆናል የተባሉ፤ ሀቅነት የጎደለቻው የግልሰብ አስተያዮቶች ናቸው፡፡ የእምነት ሰዎችን መጥቀስ ተገቢ ቢሆን እንኳ እርስዎ ከጠቀሷቸው በእጅጉ የሚልቀውን የነገረ ሀይማኖት አዋቂ ፈላስፋ ዘርአ ያዕቆብን ይጠቅሱ ነበር፡፡ ከአራት መቶ አመታት በፊት ጀምሮ የኖረው ይህ ሰው ከአክሱም ወጥቶ ተከዜን ተሻሯል፡፡ ከተከዜ ተሻግሮም የኖረባቸውን ሰዎች “የአማራ ሰዎች” እያለ ነበር የጠቀሳቸው፡፡ ከዚህ ሰው የሀይማኖት እውቀት አንጻር እና ከጊዜውም ርቀት ዋጋ የተነሳ የእርሱን ዘገባ መቀበል የግድ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ነገር እዚሁ ጽሁፍ ላይ አንድ የጎጃም ሰው እንዲህ አለኝ ብለው የዛን ሰው ቃል እንደመደምደሚያ ተጠቀሙበት፡፡ ከዛም የወሎ ሰፋሪዎች ብለው አከሉበት፡፡ በእውነቱ ይህ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ አንድ ሳይንሳዊ ጥናት ቢያንስ መረጃው ሞልቶ ድግግሞሽ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ አዋቂ ሰዎችን እየፈለገ ማናገር እንዳለበት ያሰምርበታል፡፡ መጀሪያ ብዙ አዋቂ ሰዎችን አፈላልጎ ማግኘት፤ እነሱን በተለያየ አንግል እያመሳከሩ መጠየቅ፤ የታሪክ ድርሳናትን ማገላበጥ፤ እና ያንን የተገኘውን መረጃ በጥንቃቄ አመሳክሮ መተርጎም፤ መተንተንና ድመዳሜ ላይ የሚደርስ ነገር ከሆነ መደምደም ካልሆነ ግን ጥያቀውን ለሌላ ሰው ክፍት አድርጎ መተው የሚሉት ናቸው ዋነኛ ሳይንሳዊ የጥናት ሂደቶች፡፡ እርስዎ ግን ከቃለ ምልልሱም ሆነ ከጽሁፍዎ እንደተረዳሁት ወደጥናት የገቡት መጀመሪያ ደምድመው ነው የሚመስለው፡፡ የለም ብሎ ድምዳሜ ለመድረስ ብዙ ድካም የሚጠይቅ ነው፡፡ የለም የሚል ውጤት ላይ ቢደርሱ እንኳ ከእርስዎ የተለዩ በርካታ አጥኝዎች እስኪያረጋግጡት እና ተመሳሳይ ግኝት ላይ እስኪደርሱ ከመናገር መቆጠብ ተገቢ ነበር፡፡ ምናልባት እንደደንቡ ይመስለኛል ቢሉ ትንሽ የሚመስል ነገር ይሆን ነበር፡፡ ግን ከስሁት ዘዴ ተነስተው የደረሱበት ስሁት ድምዳሜ ነው፡፡

እርስዎ መቸም የአማራ ጉዳየይ ምሁር አይደሉም፡፡ ብዙ ጽሁፎችዎን እንዳነበብኩት ፖለቲከኛ ነዎት፡፡ የፖለቲካ ፍልስፍናወ ደግሞ ሁለንተናዊ ሰውነት ዝቅ ሲልም አንድ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይህ በራሱ ክፋት የለውም፡፡ ችግሩ በዚህ ሚዛን እየለኩ አማራን አለና የለም ማለትዎ ነው፡፡ እንደኔ እይታ የእርስዎ አማራ የለም ድምዳሜ ተቀባይነት ያገኘው በአማራ ላይ ባደረጉት ልዩና ረጅም ጊዜ የወሰደ ምርምር ሳይሆን በሌላው ዘርፍ ባለዎት እውቅናና ተሰሚነት ተጠቅመው ነው፡፡ በእርስዎ የስም ክብደት ነው አማራ የለም የሚለውን አስተሳሰብ ማስረጽ የቻሉት፡፡ ዋናው ቁም ነገር የእርስዎ አለና የለም የሚል ድምዳሜ አልነበረም፡፡ ግን እርስዎ ትልቅ ስም ስላሎዎት አማራን ለመካድና ለመጉዳት ለሚደረገው ርብርቦሸ የእርስዎ ቃል በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀሰ ጥቅም ላይ መዋሉ ነው፡፡ ይህም አማራ የለም የሚለው ትርክትዎ በአንድ ወገን አማራው በአማራ ዙሪያ መሰባሰብን እንደነውር እንዲቆጥር አደረገ፡፡ በሌላ ወገን አማራ አለ በማለት ጉዳት የሚያደርሱብት ቡድኖችና ድርጂቶች የእርስዎን ቃል እንደ ይለፍ ይጠቀሙበታል፡፡ አማርኛ ተናጋሪ በሚል ድንግርግርም የሚናገርለትና ብሶቱን የሚረዳለት አጣ፡፡ የእርስዎ ሀሳብ ተከታይ የሆኑትም ለአማራ መመቻ እንጅ መመከቻ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ወያኔ በእነርሱ ንዴት አማራን ይመታል፡፡ እነሱ ግን አማራ የለም የሚሉ ናቸውና ይህ አማራ ላይ የሚያርፍ ዱላ የማይሰማቸው ሆነ፡፡

ከመአዛ ብሩ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

እንደተለመደው ሁሉ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ አማራ የለም አሉ፡፡ ደመደሙ፡፡ በጣም የሚገርመው ጥናት አጥንተው ነው የደመደሙት–እንደተናገሩት፡፡ ግን የጥናትዎ ውጤት ስለ አማራ ህልውና ሳይሆን ስለኢትዮጵያ ህልውና መሰለኝ፡፡ እንዳሉት ያገኙት ገኝት ሶስት ሀይሎች አሉ፡-እነርሱም አካባቢ፡ ሀይማኖት እና ቋንቋ ናቸው፡፡ አንዱ ሲላላ እንዱ እየወጠረ ኢትዮጵያን ጠብቆ ኖረ ነው፡፡ እግዜር ይይልዎትና ይሄ ከአማራ መኖርና አለመኖር ጋር እንዴት እንደሚገናኝ አላውቅልወትም፡፡ አማራ የሚባል ነገር የለም አሉ፡፡ ከማስረጃዎችዎ አንዱ ወሎና ጎንደር፡ ወሎና ጎጃም ምን ያገናኛቸዋል ነው፡፡ ሁለተኛው ሀረር ውስጥ አማራ የሚባሉት ክርስቲያኖች ናቸው ነው፡፡ ሶስተኛው ጎንደር ውስጥ የእስላም መንደር ምናምን የሚባል አይቻለሁ ነው፡፡ አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

ወሎና ጎንደር እንዲሁም ወሎና ጎጃም ምን ዝምድና አላቸው ሲሉ የምርዎትን ነው? አንድ ኢትዮጵያ አንድ ነው ብለዋል እዛው ቃለ መጠይቅ ላይ፡፡ ሰው አሁንም እየተጋባ እየተዋለደ ነውና አንድ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሆና ሳለ እንዴት ጎጃምና ወሎ፡ ወሎና ጎንደር ዝምድና ሳይኖራቸው ቀረ? በጣም ያስተዛዝባል፡፡ እዚህ ላይ ከቃልዎ ባሻገር የንግግርዎ ድምጸት ራሱ የሚናገረው አሉታዊ ነገር አለ፡፡ በሞቴ ዝምድና ስንት አይነት ነው በመጀመሪያ? በየትኛውስ የዝምድና መስፈርት እነዚህ ህዝቦች ሳይዛመዱ ቀሩ? ሀቁ ይህ አይደለም፡፡ ምናልባት ወሎ ውስጥ የአገውና የኦሮሞ መኖር ይሆን አማራ የለም ያስባለዎት? እንደዛ ከሆነ ደግሞ ሁለት አካባቢዎች ብቻ ናቸው ድብልቅ ማንነት ያላቸው፡፡

ንግግርዎ የሳይንስ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እውነታው እንዲህ ነበር መቀመጥ የነበረበት፡-“ወሎ ውስጥ ውስን አካባቢዎች ድብልቅ ቋንቋና የዘር ሀረግ ያላቸው አካባቢዎች አሉ፤ የተቀረው ግን አማራ ነው፡፡” እውን እርስዎ እንደሚሉት የሁለቱ አካባቢዎች ህዝብ ቁጥር ከአማራው በልጦ አማራ የለም የሚያሰኝ አልነበረም፡፡ የዘነጉት ነገር ወሎም ሆነ ጎንደር ወይም ሸዋ ወይም ጎጃም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሄረሰቦች በጣም አንድ አይነቱ ነው፡፡ ምናልባት አካባቢያዊ ዘይቤዎችና ልማዶች ከመኖራቸው በቀር በዋና ዋና መስፈርቶች አማራ ከጫፍ እስከጫፍ አንድ ነው፡፡ በቋንቋ፡ በሙዚቃ፡ በስነቃልና በስነኪን፡ በመልክ፡ በባህርይ፡ በልማድ፡ በታሪክ፡ በመሬትና የአየር ንብረት ጸባይ፡ በምርትና አመራረት፡ በስነልቡና፡ በጠቅላላ እይታ-አለም (worldview): ለረጅም ዘመናት እንደአንድ የፖለቲካና ሚሊታሪ ማህበረሰብ መኖሩና በመሳሰሉት ዋና ዋና አሃዶች ልዩነት የለውም፡፡ እርስዎ ምኑን እንደሆነ አይዛመድም ያሉት ለሰሚው ግራ ነው፡፡ እስኪ በምን በምን አሃዶች የማይዛመድ ሆኖ እንዳገኙት ያስቡና ያብራሩ፡፡ ይሄ የለም ያሉት ዝምድናስ አብሮ መኖርን ሲከለክል፤ ጋብቻን ሲከለክል አዩት? በሀሳብ ተለያይተው ቁርቁስ ውስጥ ሲገቡ አዩ? በቋንቋ ሲለያዩና ሳይግባቡ ሲቀሩ አዩ? በባህርይና በተክለቁመና ሳይመሳሰሉ ሲቀሩ አዩ? እንዴው ምን ልዩነት አዩ?

እዚህ ላይ የእምነት ጉዳይ ጠቅሰዋል፡፡ የአንጾኪያ ሰዎች አማሮች አይባሉም፤ እስላሞች ናቸው የሚባሉት ብለዋል፡፡ እንዴ ፐሮፍ.? አንድ ህዝብ ሲጠራ እኮ ከአንጻራዊ ስፍራ ነው፡፡ ማለትም ለምሳሌ እርስዎ የአዲስ አበባ ሰው ነዎት፡፡ ከኢትዮጵያ አንጻር የጉምዝ ወይም የጋምቤላ ኢትዮጵያዊያንን አይመስሉም፡፡ መልክዎ ከወደ ሰሜን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ እርስዎን የሰሜን ሰው ነው የሚልዎት፡፡ ከቆሙበት ቦታ አንጻር ፈካ ያለ ገጽታ ያለው የሰሜን ሰው ነዎት፡፡ ወደ ዩጋንዳ ቢሄዱ አንድ ዩጋንዳዊ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው የሚልዎት፡፡ እርስዎ፡ ዶር. ነጋሶ ጊዳዳ እና ሽፈራው ሽጉጤ ጉምዝ ውስጥ ብትሄዱ ሶስታችሁም አማራ ናችሁ፡፡ ደቡብ ኦሞ ውስጥ ብተሄዱ ሁላችሁም አማራ ናችሁ፡፡ ሱማሌ ብትሄዱ ሁላችሁም አማራ ናችሁ፡፡ አፋርም ብትሄዱም እንደዛው ነው፡፡ እና የአንጾኪያ ሰዎች እስላም ናቸው መባሉ ምንድን ነው ግርታው? ሁሉም አማሮች ስለሆኑ እስላም አማራና ክርስቲያን አማራ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ አይጠራሩበትም፡፡ ምክንያቱም አማራ ዋናው ማንነት ስለሆነ በዛ መጠራራት አይቻልም፡፡ ክርስቲያኖቹ በተለምዶ አማራ ነን ይላሉ፡፡ ያ ማለት ግን እስላሞቹ አማራ አይደሉም ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት ከግራኝ ጦርነት ጋር ተያይዞ የሰለሙትን አማሮች ከአማራነት ወጡ የማለት አዝማሚያ የያዘ አጠራር ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ከሆነ እስላም ማለት ምን ሊሆን ነው? ነው ወይስ ክርስቲያን እና እስላም የሚባሉ ብሄረሰቦች ናቸው ሊሉ ፈልገው ነው? አማራ አማርኛ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ ነው ብለው ስለሚምኑ እንደዛ ካሰቡ እንኳ እነዚህ የገጠር መንደሮች ዋና ከተማ ሆነው አያውቁምና እንዴት ሆነው ከማን ር ተቀላለቀሉ? እንደሚታወቀው የአንጾኪያና አካባቢው ህዝብ ለዘመናት ራሱን ከአጎራባች ብሄረሰቦች ወረራ ሲከላከል የኖረ ነው፡፡ ይህም ድብልቅነቱን እና የቋንቋ ብቻ ማንነቱን የሚያመለከት ሳይሆን ወጥነቱን ነው የሚያመለክተው፡፡

እሽ የሸዋን አማራ አለመሆን ለማረጋገጥ የአንጾኪያ ቀበሌ እስላም መባል በቂ ሆነልዎት፡፡ ምናለበት መላውን ሸዋ ወስደው አንጾኪያን ቢለኳት፡፡ ቢባል ቢባል እንኳ የአንዲት ቀበሌ ህልውና ነው የአብዛኛውን አንድ ክፍለ ሀገር ህዝብ አለመኖር ለማረጋገጥ መዋል ያለበት ወይስ ናሙና መወሰድ የነበረበት ከትልቁ ነው፡፡ የሳይንሱ የአጠናን ዘዴ ግን ከአብዛኛውም ከአነስተኛውም ወካየይ ናሙና መውሰድ እንደሚገባ ነው፡፡ ከመቶው የመላው ሸዋ አስር ድምጽ ቢወስዱ፡ ከአስሩ አንጾኪያ አንድ ይወስዳሉ ማለት ነው፡፡ ይህ የሳይንሱ ህግ ነው፡፡ በሁለተኛ ይሄም አላስኬድ ሲልዎት ወደሀረር ሄዱ፡፡ የወሎና ጎንደርን፡ የወሎና ጎጃምን አለመዛመድ ለማስረዳት ሀረር ሄዱ፡፡ ይሄን ጎንደር ሊሄዱ ጠዳ ተሸኙ እንለዋለን፡፡ ሀረር ውስጥ ያሉት ድብልቆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም አማራ ከማለት ምናልባት ክርስቲያኖች ብሎ መጥራት ተገቢ ሆኖ ይሆናል፡፡ አማራው በታሪክ አጋጣሚ ባህሉ የሁሉም ስለሆነ የአማራውን ዋነኛ መገለጫ ክርስትና ቢሰጡአቸው ምኑ ያስገርማል? ደግሞስ የዚህ አካባቢ ልዩ ተጨባጭ ሁኔታ እንጅ የወሎ፡ ጎንደርና ጎጃምን አማራ አለመሆን እንዴት ብሎ ለማረጋገጫ ይቀርባል? ሌላው ክፍተት ደግሞ ከአንድ ወገን ብቻ የሚሰበሰብ መረጃ ተአማኒ አይደለም፡፡ ክርስቲያኖቹ እነዛ እስላሞች ናቸው አሉ ብለዋል፡፡ በጀ፡፡ እስላሞቹስ ራሳቸውን ምን ብለው እንደሚረዱና ምን ብለው እንደሚጠሩ ጠይቀዋል? ክርስቲያኖች አማሮችን ምን ብለው እንደሚጠሯቸውስ መጠየቅ አልነበረብዎትም? በእርግጥ ከሁለቱም ወገን መረጃ መሰብሰብ ነበረብዎት፡፡ የሁለቱንም ወገን እርስዎ እንደሶስተኛ ወገን ሆነው ተርጉመውና አጣጥመው መደምደም ነበረብዎት፡፡ ግን መረጃዎ ሚዛናዊ ስላልሆነ ድምዳሜዎም ሚዛናዊ አይደለም፡፡ ስለዚህ የተናገሩት ነገር አይረባም፡፡ ለምን ቢሉ የጥናቱ ዘዴ ካልረባ መደምደሚያውም አይረባም፡፡

ሶስተኛው ደግሞ የአማራ አለመኖርን ያረጋገጡበት መንገድ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ጎንደር ውስጥ የእስላም መንደር ምናን የሚባል አይቻለሁ አሉ፡፡ ምነው ፕሮፍ. ምናምን አይቸ ተብሎ የህዝብን ህልውና የሚመለከት ከባድ ነገር ድምዳሜ ላይ ይደረሳል እንዴ? የጤና አልመሰለኝም፡፡ የእስላም መንደር ምናምን የሚባል አይቸ አማራ አለመኖሩን አረጋገጥኩ ብለው መናገርዎ በእውነቱ ለትልቅነትዎ የሚመጥን አይደለም፡፡ እውነቱ ጎንደር ዋና ከተማ በነበረች ጊዜ አከፋፈልዋ እንዲህ ነበር፡- ሸዋ ሜዳ–የሸዋ ሰዎች የሚያርፉበት፤ ትግሬ መጮሂያ–የትግሬ ሰዎች የሚያርፉበት፤ እስላምጌ–እስላሞች የሚኖሩበት፤ አዲስጌ–ፈላሾች የሚኖሩበት፤ ወለቃ–ፈላሾች የሚኖሩበት፤ አቡን ቤት–የካህናት አካባቢ፤ መሀል ላይ የነገስታቱ መቀመጫ ወዘተርፈ ተብላ የተከፋፈለች ነበረች፡፡ ከዚህ ሁሉ የአሰፋፈር ስምሪት የእስላም መንደር መኖሩ ብቻውን የአማራን አለመኖር ማረጋገጫ ሆነልዎት፡፡ ይህ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ሀይማኖት ራሱ የነገድ ወይም ጎሳ መለኪያ ሆኖ አያውቅም–በጭራሽ፡፡ በእርስዎ አረዳድ እስላም ስላልሆኑ ብቻ የአሌክሳንድሪያ ግብጾች ግብጻዊያን አይደሉም ማለት ነው፡፡ ካቶሊክ ኖርዲኮች ፕሮቴስታትንት ስላልሆኑ ኖርዲክ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ብዙም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ግን ነገር ያረዝማል፡፡

በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ሁለት ጊዜ ስሜት የሚለውን ቃል አነሱ፡፡ አንዱ አማራ የሚባል አንድ አይነት ስሜት ያለው ህዝብ የለም ብሏል ብለው የዶናልድ ሌቪኒን ድምዳሜ ያለምንም ማንገራገር አምነው የተቀበሉበት ነው፡፡ ስሜት ብቻ ነው እንዴ የአንድ ህዝብ አንድነት መለኪያው? አንድ አይነት ስሜት የለውም ለማለት ስንት አይነት መለኪያዎች ተወስደው ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰው? አንድ አይነት ስሜት ማለት ምን ማለት ነው? እንዴያው በሞቴ የአንድ እናትና አባት ልጆች እንኳ በስሜት ደረጃ አንድ አይነት ናቸው? በእርግጥ እርስዎ አማራ ላይ የፈለጉት የስሜትም ይሁን የምንም ነገር አንድነት በአንድ ሰው ብቻ የሚገኝ እንጅ በ35 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ የሚገኝ አይደለም፡፡ እርስዎ የፈለጉትን አይነት ስሜት ማግኘት የሚቻለው አንድ ሰው ላይ ብቻ ነው፡፡ ለዛውም የአንድ ሰው ስሜት ራሱ በየጊዜው ተለዋዋጭ ስለሆነ ረዘም ላለ ጊዜ ከተከታተሉት አንድ አይነት ስሜትና ባህርይ አይደለም ያለው፡፡

ሌላው ስሜት የሚለውን ቃል የተጠቀሙት አማራ አለመኖሩን ያረጋገጡት በስሜት አለመሆኑ ለማጤን ነው፡፡ እዚህ ላይ መክሽፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ በሚባለው መጽሀፍዎ የስሜትን ጠቀሜታ አትተዋል፡፡ ራስዎ እንደጻፉት ስቬን ሮቢንሰን የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ አዋቂ ነኝ የሚል ብለው የወረፉት የባህር ማዶ ዜጋ አለ፡፡ እርሱም አንድ ቀን ታሪክ ስትጽፍ ስሜትህ ይንጸባረቅበታል አይነት ነገር ተናገረዎ፡፡ እርስዎም እርሱ ስለኢትዮጵያ ሲጽፍ ስሜት የሌለው ኢትዮጵያዊ ስላልሆ፤ እርስዎ ግን የራስወን አገር ሲጽፉ ስሜት እንደሚኖርና ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰው “ልኩን” ነገሩት፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ችግሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ሲሆን ስሜት አለዎት፡፡ ለአማራ ሲሆን ደግሞ ምንም ስሜት የለዎትም፡፡ ለኢትዮጵያ ስሜት ስላለዎ በስሜትም በእውቀትም ተከራከሩላት፡፡ ለአማራ ደግሞ ስሜት ስለሌለዎ “ከስሜት በጸዳ” ምክንያታዊነት ካዱት፡፡ አንዱን ፈረንጅ አማራ አንድ አይነት ስሜት የለም ሲል ለምን እና እንዴት ሳይሉ ተቀበሉ፡፡ ስለኢትዮጵያ ሲጽፍ አላግባብ ተይቧል ያሉትን ፈረንጅ ግን ቁም ስቅሉን አሳዩት፡፡ ከዚህ ተነስቸ እንዲህ እደመድማለሁ፡፡ አማራን ሲክዱት የኖሩት ለአማራ ስሜት ስለሌለዎ ነው፡፡ ለአማራ ስሜት እንዳይኖረዎ ያደረገ ደግሞ አንዳች ነገር አለ፡፡ በስሜት ስለማይጋሩት ህዝብ መጻፍዎ ታዲያ የማይመለከተዎትን ነገር ልወክል ማለት አስመሰለብዎ፡፡ ሲጀመር ይህን አታጥና ይሄን አጥና ተብሎ ሰው ገደብ አይጣልበትም፡፡ አማራን ማጥናት መብትዎ ነበር፡፡ ግን በወጉ አላጠኑትም፡፡ ቢያጠኑ እንኳ ለህዝቡ ያለዎ የስሜት ቀረቤታ የጥናትዎ ውጤት ላይ ያጠላበታል፡፡ እዚህ ላይ የእርስዎ ቦታ በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን ለቅኝ ገዥዎች የማህበረሰቡን ባህልና ስነልቡና እያጠኑ የሚሰጡ ጸሀፍትን ይመስላል፡፡

እዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ በኦሮሞ ዘር ቋንቋ ነው፤ በወለጋ ዘር ቋንቋ አይደለም አሉ፡፡ ይህ ማለት ኦሮሞ ማለት ኦሮምኛ የሚናገር፤ ቋንቋውን እንደዘር ማንነት መገለጫ የሚጠቀም ማለት ነው የሚል ይዘት ያለው ነው–እንደተረዳሁት፡፡ በዚህ አረዳድ በእርግጥ ለአማራ ቋንቋ ማለት አማርኛ ማለት አይደለም፡፡ ለአማራ አማራ ማለት አማራ ብቻ ነው፡፡ ለምን ቢባል አማርኛን አማራ ያልሆኑ ሌሎችም ስለሚገሩት ቋንቋው የአማራነቱ መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባት አማራነቱ የሚታወቀው በቋንቋው ቢሆን እንኳ አማራ ብቻ የሚናገራቸው አካባቢያዊ የአማርኛ ዘይቤዎች ነው የሚሆነው፡፡ እዚህ ላይ ነው እግዲህ የእርስዎ “አማርኛ ተናጋሪ” እና የእኛ አማራነት ልዩነቱ፡፡ አማራ ያልሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎችም ስላሉ አማራው ራሱን በቋንቋው ተመስርቶ ትርጉም ሊሰጥ አይችልም፡፡ ልክ አሜሪካዊያን እንግሊዝኛ በመናገራቸው ብቻ የኢንግላንድ ተወላጆች ሊሆኑ እንደማይችሉት ሁሉ፡፡

እና ቃለ ምልልሱ ላይ እንደተረዳሁት ሀረር የተገደሉት አማሮች ሳይሆኑ የሰላሌ ኦሮሞዎች ናቸው አሉ፡፡ አማራ አለመሆናቸውን እንዴት አወቁ ታዲያ? አማራ ከሌለ ሀረር የተገደሉት እንዴት ሆነው ነው አማራ ያልሆኑት? ምናልባት ኦነግ እነዛን ሰዎች ሲገድል የሸዋ ኦሮሞ ኦሮሞ አይደለም ብሎ ነው የገደላቸው ወይስ አማራና ኦሮሞ መለየት አቅቶት ነው? እዚሁም ላይ የሰላሌን ሰው ኦሮሞነት ሳያቅማሙ ተቀብለው ሲያበቁ አማራን ግን አማራ ለማለት ተናነቀዎት፡፡ እዚህ ላይ የኢሰመጉ መሪ ስለነበሩ አማራ አይደሉም የተገደሉት አልኩ አይነት ነገር ብለዋል፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ሀጢአት ሰርተዋል ብየ አስባለሁ፡፡ በወቅቱ አማራ እየተገደለ ነው ብለው ተናግረው ቢሆን ኖሮ ከዛ ወዲህ እስካሁን የሚገደሉት አማሮች ቁጥር ይቀንስ ነበር ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ በቀጥታ አማራ ተገደለ ብለው ቢሆን ኖሮ አገዛዙም ከዛ ወዲህ የሌላውን አማራ ተቃውሞ በመገንዘብ ጠበቃ ሊያደርግ ይችል ነበር ብየ አስባለሁ፡፡ ግን የኢሰመጉ ሀላፊ ሆነው የተገደለው አማራ አይደለም ማለትዎ መቸም አሉታዊ ተጽእኖ አልፈጠረም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ኦሮሞ የሆነው ኦነግ አማራ ብሎ ገደላቸው፡፡ እርስዎ ደግሞ አማራ አይደሉም አሉ፡፡ በግርግሩ ምናልባት ከለላ ሊሆናቸው የነበረ አካል ከነበር እጅና እግሩን አሰሩት ብየ እገምታለሁ፡፡ ለኦሮሞ የሚታገል ኦነግ አማራና ኦሮሞ መለየት አቅቶት ኦሮሞ ገደለ ማለትዎ መቸም ማንን እደሚያሳምን አላውቅም፡፡ ኢሳት ላይ የቀረበ የአንድ ከዛ ፍጅት የተረፈ መነኩሴ ቃለመጠይቅ አለልዎት እና ይዩት፡፡ ያ መነኩሴ ስለማን እንደሚያወራ እና እርሱም ማን እንደሆነ እርስዎ በደምሳሳው ከሚክዱት የበለጠ ተአማኒነት አለው፡፡ ከእርስዎ ይልቅ ትክክለኛውን የታሪክ ተሳታፊ ለማመን እገደዳለሁ፡፡

እንደ መደምደሚያ

አንድ ህዝብ ጎሳ የሚሆነው በውስጣዊ እምነቱና ስሜቱ ብቻ አይደለም፡፡ የውጫዊ ግፊቶችም አንድን ህዝብ ቅርጽ የመስጠት አቅም አላቸው፡፡ በዚህ አንግል ካዩት አማራ ከኦሮሞ መስፈፋፋት ጋር ሲፋሎም የኖረ ነው፡፡ ይህም ውጫዊ ግፊት የውስጥ አንድነት እንዲፈጥር አስገድዶታል ማለት፡፡ ይህንን ውጫዊ ገግፊት የተከሰተበትን ጊዜ ብንወስድ እንኳ አራት መቶ አመት ይሆነዋል፡፡ አንድን ጎሳ ለመፍጠር ደግሞ ይህ ክስተት ብቻውን ከበቂ በላይ ነው፡፡ ችግሩ ብዙዎች ስለአማራ ሲናገሩ ከአለም ህዝብ በተለየ ሁኔታ አማራ እስከ አዳምና ሄዋን የደም ሀረግ እንዲመዝ መፈለጋቸው ነው፡፡ ይህ ግን አንድን ጎሳ ሊፈጥሩ የሚችሉት ሁለት አመክንዮዎችን የጣሰ ነው፡፡ አንዱ እኔ በደሜ አማራ ነኝ ብሎ ማመን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጠቀስኩት ውጫዊ ግፊትና ይህንን ግፊት ተከትሎ የሚመጣው ፖለቲካዊ ቅርጽ ነው፡፡ አማራ በትውልድም አማራነቱን ያምናል፡፡ እርስዎ አዲስ አበባ በመወለድና ማደግዎ ብዙ የማያውቁት ነገር እንዳለ እገነዘባለሁ፡፡ እኔ ደግሞ ከመሀሉ ስለተወለድኩ አውቀዋለሁ፡፡ አማራ ሲጋባ እስከሰባት ቤት ይቆጥራል–ወደኋላ፡፡ ወደጎን ደግሞ “አጥንተ ሰባራ” እና “ጨዋ” የሚሉትን የማንነት መገለጫዎች ያጣራል፡፡ የዚህ እሳቤ ጥንካሬው እርስዎ ከሚገምቱት በላይ ነው፡፡ ዝርዝሩን አልናገረውም፡፡ ካወቁት ያውቁታል፤ ካላወቁትም ሩቅ ነዎት ማለት ነው፡፡ ወሎ፤ ጎጃም፤ሸዋ፤ ጎንደር ዝምድና የላቸውም ያሉት ትርክት በጣም የማይረባ ነው፡፡ ለዘመናት ሲደጋገሙ የኖሩ የወታደራዊ፤ የንግስና ሽኩቻና መሳፍንታዊ ዝውውሮች ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡ ሁሉም የአማራ ክፍለ ሀገሮች ተራ በተራ አንዱ አንዱን ሲወረው፤ አንዱ አመጸኛ ሰራዊቱን ይዞ ወደሌላው ሲሸሽ፤ እና የመሳፍንቱም ጦር በየጊዜው ኡደታዊ ሰፈራ ሲያደርግ ነው የኖረው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ አማራ ሊገለጽ የማይችል የእምነት፤ የባህርይ፤ የታሪካዊ ውርስ፤ የስነልቡና፤ የአኗኗር ዘዴ፤ የልማድ፤ የስነጥበብና ቋንቋ ወዘተርፈ አንድነት እንዲኖረው አስቻለ፡፡

በመጨረሻም አማራ የለም ባሉበት አንደበትና ብእርስ ምነው ትግሬ ወይም ኦሮሞ አለመኖሩን ሳይጽፉ ቀሩ? ምናልባት የአማራን አለመኖር ለማነጻጸር አጎራባች ጎሳዎችን መዳሰስ አልነበረብዎትም? በእርግጥ አማራ የለም የሚለው ትርክት ምን ጥቅም ያመጣል ብለው አስበው ነው? አሁንስ የጥናትዎን ዘዴ ደካማነት ለመፈተሸና ድምዳሜዎን እንደገና ለማየት ወኔው አለዎት ወይ?


No comments:

Post a Comment