Friday, May 22, 2015

የአየር ሃይልና የመከላከያ አባላት ክስ ተመሰረተባቸው

ሚያዝያ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል፤ አባላትን መልምለዋል፤ ለሽብርተኛ ቡድኑ መረጃ አቀብለዋል፤ እንዲሁም ወደኤርትራ በመኮብለል የሽብር ድርጅቱን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ተሰናድተው ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ በሚል የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በ7 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ግንቦት 11 ቀን 2007 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መመሰርቱን ሰንደቅ ዘግቧል።ተከሳሾች መቶ አለቃ ማስረሻ ስጤ፣ መቶ አለቃ ብሩክ አጥናዬ፣ መቶ አለቃ ዳንኤል ግርማ፣ መቶ አለቃ ገዛኸኝ ደረሰ፣ ተስፋዬ እሸቴ፣ ሰይፉ ግርማ እና የሻምበል አድማው አዳሙ መሆናቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።“ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፈራረስ ዓላማን ይዘው ለማስፈፀም እና በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፤ ህብረተሰቡን ለማስፈራራት፤ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማት ለማናጋትና ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሰውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ከተባለው የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል በመሆንና በሽብር ድርጅት ለመሳተፍ ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ” የሚል ክስ እንደቀረበባቸው
ጋዜጣው ዘግቧል። ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ በ2006 ዓ.ም ከሽብር ድርጅቱ ከፍተኛ አመራር በሆነው ሻለቃ አክሊሉ መዘነ አማካኝነት በህቡዕ ተመልምለው አባላትን እንዲመለምሉም ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ይንቀሳቀሱ ነበር ብሎአል አቃቢ ህግ።ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው ከአፌዲሪ መከላከያ የአየር ኃይል ንብረት የሆኑ አንድ-አንድ ማካሮቭ ሽጉጥና 16 ጥይቶችን ይዘው በመውጣትና በመሸጥ፤ እያንዳንዱ አንዱን ማካሮቭ በ2ሺህ 500 ብር እንዲሁም እያንዳንዳቸው የያዙትን 16 ጥይቶች በ240 ብር ዋጋ በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው በማዋል በፈፀሙት ወታደራዊ ትጥቅና መሣሪያዎችን ያለአግባብ መገልገል ወንጀልም መከሰሳቸውን ጋዜጣው ጠቅሷል።ሻንበል አድማው አዳሙ ከኢፌዲሪ አየር ኃይል ድሬዳዋ ቅርንጫፍ የሆነ አንድ ማካሮቭ ሽጉጥ ከ8 ጥይቶች ጋር በ33 ሺህ 700 ብር በመግዛቱ በፈፀመው በከባድ ሁኔታ የመሸሸግ ወንጀል መገሰሱ ተዘግቧል። ተከሳሾች የዋስትና መብታቸውን ተነፍገዋል። ሁሉም ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ለማዳመጥ ለግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። ተከሳሾች በማእከላዊ እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው መዘገባችን ይታወሳል። ጄ/ል ሳሞራ የኑስ እስረኞችን በድሬዳዋ አየር ሃይል ግቢ በማዞርና ቪዲዮ ቀርጾ በማሳየት ሌሎች የአየር ሃይል ባልደረቦች የእነሱን እግር ቢከተሉ ተመሳሳይ እጣ እንደሚገጥማቸው ሲዝቱ ነበር። በአየር ሃይል ውስጥ ያለው አለመረጋጋት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ ድርጅቱን ጥለው ለመውጣት የሚጠባባቁ በርካታ አባላት እንዳሉ የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ። በአየር ሃይል አባላትና በመንግስት መካከል አለመተማመኑ በጨመረበት በዚህ ሰአት፣ መንግስት ወታደሮችን ለመደለል ከቤትና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት ለማረጋጋት እየተንቀሳቀሰ ነው።


No comments:

Post a Comment