Friday, May 1, 2015

በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች ከምርጫው በፊት ውሳኔ አያገኙም ተባለ

ሚያዝያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከደህንነት ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ሚያዚያ 30 ፣ 2007 ዓም ከፍተኛው ፍርድ ቤት በእነ አቶ አቡበክር አህመድ በተከሰሱት ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከደህንነት መስሪያ ቤት በተሰጠትእዛዝ፣ ውሳኔው ከምርጫው በፊት አይሰጥም። ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ የተባሉት የደህንነት ባለስልጣን ይህንኑ አቋም በቅርቡ ተደርጎ በነበረው የኢህአዴግ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

ውሳኔው በተያዘለት ቀን እንዳይሰጥ የተፈለገው፣ ውሳኔውን ተከትሎ ሙስሊሙ ሊያሰማ የሚችለውን ተቃውሞ ለመቀነስ ነው። ለውሳኔው መራዘም ዳኞች ስልጠና ገብተዋል የሚል ምክንያት ሊሰጥ እንደሚችልም መረጃው አመልክቷል።



በመሃል ዳኝነት የሚሰሩት የኢህአዴግ አባሉ ሙሉጌታ ሲሆኑ፣ እርሳቸው ከደህንነት መስሪያ ቤት የሚሰጣቸውን ትእዛዝ በቀኝ ዳኛው በአቶ አለማየሁና በግራ ዳኛው አቶ ባህሩ ላይ ተጽእኖ በማሳረፍ ሁለቱ ሰዎች ተጽፎ በሚመጣው ውሳኔ ላይ እንዲፈርሙ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

አቶ አለማየሁ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ውጭ አገር ሄደው ለመታከም ማመልከቻ ቢያስገቡም፣ ውሳኔውን ሳይፈርሙ እንደማይሄዱ ተነግሮአቸዋል። በእስር ላይ የሚገኙት የኮሚቴው መሪዎች በሃሳብ እንዲከፋፈሉ የተለያዩ እቅዶች መዘርጋታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ቀደም ብሎ መሪዎችን  በሽምግልና ለመፍታት ተደርጎ የነበረው ሙከራ በእስር ላይ ያሉት መሪዎች ” ይዘውት የተነሱት ጥያቄ ካልተፈታ የእነሱ መፈታት ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ” መናገራቸው እንዲሁም ፣ የደህንነት መስሪያ ቤቱ የሽምግልና ጥረቱ እንዲቋረጥ ግፊት በማድረጉ ሳይሳካ ቀርቷል።

በተራዘመ ፍርድ የሚሰቃዩት የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት፣ በሽብር ወንጀል ሊያስከስሳቸው የሚችል ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሊቀርብባቸው አልቻለም።


No comments:

Post a Comment