Thursday, May 7, 2015

በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ታፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወሰዱ

ሚያዝያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ተይዘው በወረዳ 5 ቀበሌ 08/09 በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉ ወጣቶች ዛሬ ጧት ላይ በሶስት አይሲዙ መኪኖች ተጭነው ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ ከየስፍራው የተሰባሰቡ ሲሆን፣ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ረብሻ ሊያስነሱ ይችላሉ በሚል በአደገኛ ቦዘኔ ስም የተያዙ ናቸው። ብዙዎች ሌሊት ሌሊት በሚደርስባቸው ድብደባ ክፉኛ ተጎድተዋል።

የአይን እማኞች እንደሚሉት እስረኞቹ ኩላሊታቸው የሚገኝበት የሰውነት ክፍላቸው አካባቢ በጫማ እየተረገጡ፣ በዱላ እየተደበደቡ እንዲሁም ውሃና ምግብ እየተከለከሉ “ተቃውሞውን ያነሳነው በሰማያዊ ፓርቲ ግፊት ነው” ብለው  እንዲመሰክሩ ጫና ተድርጎባቸዋል። የአዲስ አበባ እስር ቤቶች ሌሊት በሚታፈኑ ወጣቶች እየሞሉ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።


No comments:

Post a Comment