Wednesday, May 27, 2015

ፍ/ቤቱ በጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የቀረቡ የሲ.ዲ መረጃዎችን ውድቅ አደረገ

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ዛሬ ግንቦት 19/2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ መዝገቡ የተቀጠረው አቃቤ ህግ አሉኝ ባላቸው ሲ.ዲዎች እና ቀሪ ምስክሮቹን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ ቀሪ ምስክሮቹን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ለማቅረብ ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ የሰጠውን እድል ባለመጠቀሙ እና ምስክሮቹን ላለማቅረቡ የሰጠው ምክንያትም በቂ ባለመሆኑ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ባለመፍቀድ ከዚህ በኋላ ምስክሮቹን እንደማይሰማ አመልክቷል፡፡
አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት ይዟቸው የቆያቸውን የ12ቱን ሲ.ዲዎች ጉዳይ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሲ.ዲዎቹ በማስረጃ ዝርዝሩ ውስጥ ፕሪንት ተደርገው የተያያዙ ሰነዶችን እንደያዙ ስለተገለጸ ሲ.ዲዎቹ ከማስረጃነትም ሆነ ከኤግዚቢትነት ውድቅ መደረጋቸውን ገልጹዋል፡፡
አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የሲ.ዲ ዶክሜንተሪ ማስረጃ ማቅረቡን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትለት የጠየቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አቃቤ ህግ ሲ.ዲውን በጽ/ቤት በኩል እንዲያስገባ በማዘዝ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን ዶክሜንተሪ በቢሮ ዳኞቹና ጠበቆቹ እንዲመለከቱት ከተደረገ በኋላ ሲ.ዲው ሌሎችን ተከሳሾች ይመለከታል ወይስ አይመለከትም የሚለውን አይቶ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 8/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች ጥያቄያቸውን ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት በሞከሩበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ የመናገር እድል ሲነፈጉ የተስተዋለ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ሲጠይቁ ‹‹ስነ-ስርዓት አድርጉ!›› ባለ ጊዜ ጦማሪ አቤል ዋበላ ‹‹እናንተ ራሳችሁ ስነ-ስርዓት አድርጉ....እንናገርበት! ይህ የመብት ጉዳይ ነው...በግልጽ ችሎት ላይ ህገ መንግስታዊ መብታችንን አክብሩ እንጂ...ጥያቄ አለን ተቀበሉን›› ሲል በመናገሩ ችሎት ደፍረሃል ተብሏል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ በአቤል ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 25/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


No comments:

Post a Comment