Tuesday, May 27, 2014

በማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ረቂቅ የፓትርያርኩና የምልዓተ ጉባኤው ልዩነት ተካሯል፤ ለመሥራት ተቸግሬአለኹ ያሉት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከፓትርያርኩ ረዳት ሓላፊነት ለመልቀቅ ጠይቀዋል


ፓትርያርኩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከጨለማው ቡድንና ፖለቲከኞች ጋራ የመከሩበትን የራሳቸው ያልኾነ የተልእኮ ሐሳብና አጀንዳ የተቃወሟቸውን የምልዓተ ጉባኤውን አባላት ‹‹በገንዘብ የተገዛችኹ›› እያሉ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችና በአማሳኞች መሠረተ ቢስ ክሥና ውንጀላ በመዝለፍ ቅዱስ ሲኖዶሱን ተዳፍረዋል፡፡አቡነ ማትያስ ለአጥኚ ኮሚቴው የላኩት ባለ24 አናቅጽ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች ሳይቀነሱና ውይይት ሳይደረግባቸው በደንቡ ካልተካተቱና ረቂቁ በሌላ ኮሚቴ ዳግመኛ ካልታየ በሚል አጀንዳውን በራሳቸው አቋም ብቻ ለመቋጨት ያደረጉት ሙከራ፣ በፍጹም አንድነት በቆሙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተቃውሞ ውድቅ በመደረጉ በመተዳደርያ ደንቡ ማሻሻያ ላይ የሚደረገው የምልዓተ ጉባኤው ውይይት ይቀጥላል፡፡ከድንጋጌዎችና ግዴታዎቹ መመሪያ ውስጥ፡- የማኅበሩ ፈቃድ በየዓመቱ እንዲታደስ፤ ማኅበሩ ከቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዳይሰበሰብና ቢሮ እንዳይከፍት፤ የሠራተኞቹ ቅጥርና ምደባ በመንበረ ፓትርያርኩ እንዲካሔድ፤ አባላቱ በግልም በቡድንም በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥራ፣ በቀኖናዊ የሥነ ሥርዓት ድንጋጌና በሰንበት ት/ቤቶች ጉዳይ እንዳይገቡ፤ የማኅበሩ አባላት በግል ለሚሠሩት ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና የሀገርን ሰላም የሚፃረር ድርጊት›› ማኅበሩ ሓላፊነት እንዲወስድ የሚሉት ይገኙበታል፡፡የአጥኚ ኮሚቴው አብላጫ አባላት፣ የፓትርያርኩን የድንጋጌዎችና ግዴታዎች መመሪያ ‹‹ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔና የደንብ ማሻሻያ አቅጣጫ ጋራ የማይሔድ›› በሚል ያልተቀበሉት ሲኾን ማኅበሩ በበኩሉ በተለይ በፈቃድ ዕድሳት ረገድ የተነሣው ሐሳብ ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በጸደቀ መተዳደርያ ደንብ የሚመራውን የማኅበሩን አገልግሎት ለማስቆም የሚደረግ አካሔድ ነው፤›› ብሏል፡‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የመሥራት አቅሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ፣ በቤተ ክርስቲያናችንም እየሠራ ባለው ሥራ ኹሉ አብያተ ክርስቲያናትን፣ አድባራትንና ገዳማትን በስፋት እየጠቀመ ያለ፣ በምሁራን የታቀፈ ኹለንተናዊ ዝግጅት ያለው ማኅበር ስለኾነና ብዙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ በመኾኑ ራሱን የቻለ ድርጅታዊ መዋቅር ሊዘጋጅለት እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡›› /የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጥኚ ኮሚቴውን ባቋቋመበት የግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ/‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እያደገ በመሔድ ላይ ለሚገኘው የማኅበሩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚመጥንና ለወደፊቱም ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ዕድገት የሚጠቅም የላቀና የተሻለ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማበርከት የሚያስችለው ራሱን የቻለ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሊዘጋጅለትና የማኅበሩን አገልግሎቶችና የወደፊት ኹኔታዎች ያገናዘበ መተዳደርያ ደንብ ሊቀረፅለት ይገባል፡፡›› /የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔው ለአጥኚ ኮሚቴው የሰጠው የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ አቅጣጫ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሓላፊነታቸው በአርኣያነት የሚጠቀስ ጥረት ባደረጉበት የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ሳቢያ ከፓትርያርኩ ጋራ ውስብስብ ችግር ውስጥ እንደገቡና አብረው ለመሥራት እንደሚቸገሩ በምልዓተ ጉባኤው መካከል ቆመው የተናገሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹አባቶቼ፣ አሰናብቱኝ›› ሲሉ ቅዱስ ሲኖዶሱን ጠይቀዋል፤ ምልዓተ ጉባኤው እንደሚነጋገርበት ይጠበቃል፡፡ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መልቀቂያ ያቀረቡበትን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ለመከፋፈል እየተጠቀሙበት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ በቅርቡ ባረፉት ብፁዕ አቡነ ቶማስ ቦታ÷ ምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት÷ ተዛውረዋል፤ በምትካቸው የአኵስም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩትና የመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም የበላይ ጠባቂ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሰላማ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት መመደባቸው ተጠቁሟል፡፡

No comments:

Post a Comment