Sunday, May 25, 2014

በአውሮፕላን ጎማ ስር ተደብቆ 5 ሰአት በአየር ላይ የተጓዘው ተአምረኛ ወጣት እናት ያለችው ኢትዮጵያ ነው


ከአድማስ ራድዮ የተገኘ

ባለፈው ሰሞን ከካሊፎርኒያ ተነስቶ ሃዋይ ድረስ በአውሮፕላን ጎማ በመንጠላጠል የተጓዘው ወጣት ህይወት መትረፍ ተአምር መሰኘቱን መዘገባችን ይታወሳል። ይህ የ 16 ዓመት ወጣት ሶማልያዊ መሆኑ ሰሞኑን ሲዘገብ፣ እናቱ ደግሞ ያለችው ኢትዮጵያ መሆኑ አብሮ ተነስቷል።
ሶማሌያዊዋ እናት ምርጊቱ ከጭቃ በተሰራ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ተቀምጣለች። ግድግዳው ከመሳሳቱ የተነሳ ነፋስ እንዳያስገባ በአሮጌ አንሶላ ተሸፍኗል። ያለችው ሸደር በተሰኘ የስደተኞች መጠለያ ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እንግዲህ የካሊፎርኒያው የ 16 ዓመት ወጣት ሶማሌያዊ አውሮፕላን ላይ የተንጠለጠለው እዚህች ስደተኛ እናቱ ጋር ኢትዮጵያ ለመምጣት በመፈለጉ ነበር።

ዩባ መሃመድ የተባለችው ይህችው እናት፣ እሷን ናፍቆ አውሮፕላን ላይ ተንጠለጠለ የተባለው ይህን ልጇን ላለፉት 8 ዓመታት አላየችውም። ጸጉሯን የሸፈነችበትን ነጭና ጥቁር ሂጃብ እያሻሸች፣ ያህያ አብዲ ስለተባለው ይኸው ወጣት ልጇ ስትናገር በእምባ ጭምር ነው። ለ 5 ሰአት ተኩል በአውሮፕላን ጎማ ተንጠልጥሎ ከአገር አገር ሄደ መባልን ስትሰማ እንደተንቀጠቀጠች ትናገራለች።

ወጣቱ ያህያ አብዲ ካሊፎርኒያ ሊያሳድጉት በወሰዱት ቤተሰቦች ዘንድ ደስተኛ አልነበረም። ደስተኛ ያልሆነው በነሱ አያያዝ ሳይሆን፣ እናቱን እጅግ በመናፈቁ ነበር። እናም ናፍቆቱ ሲብስበት ባለፈው ኤፕሪል 20 ቀን ፣ ከቤቱ በመውጣት ሳንሆዜ ከተማ ባለው አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አጥር ጥሶ ገባ። እናም በልጅነት ሃሳቡ ፣ ወደ እናቱ ሊወስደው የሚችለው አውሮፕላን ነውና ፣ ያገኘው አውሮፕላን ጎማ ላይ ተንጠላጠለ። አውሮፕላኑ ደግሞ እንዳጋጣሚ ወደ ሃዋይ የሚሄድ ነበረ።


እሱ እንደተንጠለጠለ ፣ አውሮፕላኑ ተነሳ፣ ጎማውን አጠፈና ወደውስጥ ከተተ፣ ያህያ አብዲም አብሮ ውስጥ ገባ። ከዚያ በኋላ ነው አምስት ሰአት ተኩል ፣ በነጌቲቭ 50 ዲግሪና በ32ሺ ጫማ ከፍታ የተጓዘው። በዚያ ቅዝቃዜና ኦክስጅን አየር በማይገኝበት ሁኔታ በህይወት መድረሱ እጅግ ተአምር ተሰኝቷል።

“በጣም ጎበዝ ልጅ ነው ..” ትላለች ዩባ ስለልጇ ስትናገር .. “ጎበዝ ልጅ ነው፣ በጣም ይወደኛል፣ እኔን ለማየት እንደሚፈልግና እንደሚናፍቅም በልቤ አውቃለሁ። ግን አባቱ በፍጹም ከኔ ጋር እንዲገናኝ አይፈልግም፣ ለዚህ ነው “እናትህ ሞታለች” ብሎ የነገረው”
አሁን በቅርብ ግን ወጣቱ ያህያ እናቱ በህይወት መኖሯን በወሬ ወሬ ሰማ። ከዚያ ወዲህ ናፍቆቱ ባሰበት። አባቱና ሶስት ወንድሞቹ አብረውት ካሊፎርኒያ ቢኖሩም ፣ እሱ ግን ድሮም ለ እናቱ ልዩ ፍቅር ነበረው።

በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ሸደር የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ከ10ሺ በላይ ሶማሌያውያን ስደተኞች አሉ። ከነዚያ አንዷ የሆነችው የያህያ እናት የ 33 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ ላለፉት 4 ዓመታት እዚያ ቆይታለች። በስደተኞቹ ካምፕ ውስጥም አትክልት በመሽጥ ትንሽ ገንዘብ ለማግኘት ትሞክራለች።
ባለፈው ዓመት ታዲያ ከካምፑ ወጥተው ካሊፎርኒያ መምጣት የቻሉ ኡዌይ እና ጃማ የተባሉ ስደተኞች፣ ካሊፎርኒያ ክደረሱ በኋላ ለያህያና ለሌሎቹም ወንድሞችና እህቶቹ “እናታቸው በኢትዮጵያው ሸደር ጣቢያ እንደምትገኝ” ይነግሯቸዋል። በዚያ ጊዜ የተፈጠረውን ሁኔታ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ ፋቲ ሊዩኒ ሲናገሩ … “ልጆቹ በአባታቸው እንዴት ሞታለች ትለናለህ ብለው በጣም ተበሳጩ፣ አሁኑኑ ያለችበት ቦታ ካልሄድንም ብለው ተነሱ፣ አባታቸው ግን “ውሸት ነው ሞታለች” እያለ ይከራከራቸው ነበር” ነበር ያሉት።

ከዚያች ቅጽበት በኋላ ነው የ 16 ዓመቱ ወጣት ያህያ እናቱን ለማግኘት ቆርጦ የተነሳው። እናት ዩባ አብዱል ፣ ልጇ በአውሮፕላን ተንጠላጥሎ እሷን ፍለጋ መሄዱን የሰማቸው አሜሪካ ከሚኖርና ከምታውቀው ክበበው አበራ ከተባለ ሰው መሆኑን ትናገራለች። ከዚያ ወዲህ ከልጇ ጋር ለመገናኘት እሷም ውላ ማደር አትፈልግም። ሁሉም ተባብሮ እንዲያገናኛት ልመና ይዛለች።

ምኞቷም እውን ሊሆን የሚችልበት መንገድ መኖሩን የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ይናገራል። አሁን ወደ አሜሪካ ሊወሰዱ ከሚችሉ ስደተኞች መካከል አንዷ ሆና የመጀመሪያውን ቃለመጠይቅ አልፋለች:፡ ሁለተኛውን ማጣሪያ ደግሞ ካለፈች በአንድ ዓመት ውስጥ አሜሪካ ልትሄድ ትችላለች። ተሳክቶላት ከመጣችም እሷን ለማግኘት ህይወቱን አደጋ ውስጥ ጥሎ በአውሮፕላን የተንጠለጠለውን ልጇን ታገኘው ይሆናል።


No comments:

Post a Comment