Saturday, May 31, 2014

አገሪቱ በሙሉ ወደ ግዙፍ እስር ቤት በተቀየረችበት ሁኔታ  የእኔ መከሰስ አያስደንቅም 

             የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል የአመራር አባልና የቀድሞው የአማራ ክልል ወጣቶች ሊቀመንበር ዘመነ ካሴን ጨምሮ 10 ወጣቶች በተከሰሱበት የሽብረተኝነት ወንጀል ጥፋተኞች መባላቸውን ተከትሎ፣ ክሱን በሌለበት የሚሰማው አንደኛው ተከሳሽ ዘመነ ካሴ የቀረበበትን ክስ አጣጥሎታል።
አንደኛ ተከሳሽ ዘመነ ካሴ “ኤርትራ ሄዶ የጦር ስልጠና ወስዶ መምጣቱን ፣ መንግስት አሸባሪ ብሎ ከሰየመው የግንቦት ሰባት ድርጅት አመራሮች በተለይም ከጄኔራል ተፈራ ማሞ እና ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር በአካል ተገናኝቶ የሽብር ተልዕኮ መቀበሉን፣ በፌስ ቡክና በተለያዩ የኢንተርኔት ግንኙነቶች ከሌሎች አባላቱ ጋር በመገናኘትና መልዕክት በማስተላለፍ ተጠያቂ ” መሆኑን አቃቢ ህግ በክስ ማመልከቻው ላይ ጠቅሷል።
“ጄኔራል ተፈራ ማሞ በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው እስር ቤት ሲወርዱ ከስርአቱ ጋር ነበርኩ” በማለት ክሱን ያጣጣለው ዘመነ ፣ “ጄኔራል ተፈራን እስር ቤት ውስጥ አግኝተኸዋል ከተባልኩም ስርአቱን በሃይል ለማንበርከክ ከሚታገል ድርጅት ጋር ከመቀላቀሌ በፊት ከስርአቱ ጋር እያለሁ ሊያስሩኝ ይችሉ ነበር ” ብሎአል፡
“አገሪቱ በሙሉ ወደ ግዙፍ እስር ቤት በተቀየረችበት ሁኔታ  የእኔ መከሰስ አያስደንቅም ያለው ዘመነ፣ እኛ እየሞከርን ያለውን ከታሰርንበት ካቴና ተንፈራግጠን ራሳችን በማስፈታት ፣ ምናልባት ይህን አስረን ጥለነዋል የሚሉትን ትውልድ ሃይሉን አስተባብሮ ፈርገጥ እንዲልና የራሱን እጣ ፋንታ እንዲወስን” ለማድረግ ብሏል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ.ም በ 9 ኝ ተከሳሾች ላይ፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በማሴር ከጎረቤት አገሮች ስልጠና በመውሰድ፤ የጦር መሳሪያ ግዢን በመፈፀምና የሽብር እቅድ በማውጣት በተለይም በአማራ ክልል በሚገኙ ባለስልጣናት ላይ ግድያ ለመፈፀም የተከላከሉ በይን ሰጥቷል።
ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተከሳሾች ማለትም  ዘመኑ ካሴ፣  አሸናፊ አካሉ፣  ደናሁን ቤዛ፣  ምንዳዬ ጥላሁን እና  አንሙት ይሄይስ በማህበራዊ ድረ-ገፆች ግንኙነትን በመፍጠር ተልዕኮና ትዕዛዝን በመቀበልና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚረዳቸውን የመሳሪያ ግዢ እንዲከናወን ማድረጋቸውን አቃቢ ህግ ገልጿል።
“በአንፃሩ ደግሞ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያሉት ተከሳሾች ደሳለኝ አሰፋ፣  ምክትል ኢንስፔክተር ሙልዩ ማናዬ፣  ጠጋው ካሳና  ይህአለም አካሉ በሽብር እንቅስቃሴው ውስጥ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እርዳታ ሰጥተዋል” የሚለው አቃቢ ህግ፣ ከተከሳሾች መካከል10ኛ ተከሳሽ ሆና ጉዳዩዋን ስትከታተል የቆየችው ሙሉ ሲሳይ በነፃ እንድትሰናበት ተደርጓል።
ኢሳት ዜና

No comments:

Post a Comment