Thursday, May 29, 2014

በግንቦት7 ስም የተከሰሱ ጥፋተኞች ተባሉ


May 28/2014

 ኢሳት ዜና :-የግንቦት7  ህዝባዊ  ሃይል የአመራር አባልና የቀድሞው የአማራ ክልል ወጣቶች ሊቀመንበር ዘመነ ካሴን ጨምሮ 10 ወጣቶች በተከሰሱበት የሽብረተኝነት ወንጀል ጥፋተኞች ተብለዋል።

ሰንደቅ እንደዘገበው አቃቢ ህግ ተከሳሾች ከግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር በህቡዕ ግንኙነት በመፍጠር፤ ኤርትራ ድረስ በመሄድ የጦር ስልጠና በመውሰድና ተልዕኮ ተቀብለው በመምጣት በጦር መሳሪያ የታገዘ የሽብር ወንጀል ሊፈፅሙ ነበር ብሎአል።

የፌዴራሉ  ከፍተኛ  ፍርድ  ቤት  4ኛ  ወንጀል ችሎት ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ተከሳሾች እንዲከላከሉ ሲበይን፣ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ህገ-መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በማሴር ከጎረቤት አገሮች ስልጠና በመውሰድ፤ የጦር መሳሪያ ግዢን በመፈፀምና የሽብር እቅድ በማውጣት በተለይም በአማራ ክልል በሚገኙ ባለስልጣናት ላይ ግድያ ለመፈፀም አሲረው መንቀሳቀሳቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።አንደኛ ተከሳሽ ዘመነ ካሴ “በዐቃቤ ህግ ክስ ስር ከቀረቡበት ክሶች መካከል ኤርትራ ሄዶ የጦር ስልጠና ወስዶ መምጣቱን ፣ መንግስት አሸባሪ ብሎ ከሰየመው የግንቦት ሰባት ድርጅት አመራሮች በተለይም ከጄኔራል ተፈራ ማሞ እና ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር በአካል ተገናኝቶ የሽብር ተልዕኮ መቀበሉን፣  በፌስ ቡክና በተለያዩ የኢንተርኔት ግንኙነቶች ከሌሎች አባላቱ ጋር በመገናኘትና መልዕክት በማስተላለፍ ተጠያቂ ” መሆኑን ገልጿል።

ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተከሳሾች ማለትም  ዘመኑ ካሴ፣  አሸናፊ አካሉ፣  ደናሁን ቤዛ፣  ምንዳዬ ጥላሁን እና  አንሙት ይሄይስ በማህበራዊ ድረ-ገፆች ግንኙነትን በመፍጠር ተልዕኮና ትዕዛዝን በመቀበልና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚረዳቸውን የመሳሪያ ግዢ እንዲከናወን ማድረጋቸውን አቃቢ ህግ ገልጿል።

“በአንፃሩ ደግሞ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያሉት ተከሳሾች ደሳለኝ አሰፋ፣  ምክትል ኢንስፔክተር ሙልዩ ማናዬ፣  ጠጋው ካሳና  ይህአለም አካሉ በሽብር እንቅስቃሴው ውስጥ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እርዳታ ሰጥተዋል” የሚለው አቃቢ ህግ፣ ከተከሳሾች መካከል  10ኛ ተከሳሽ ሆና ጉዳዩዋን ስትከታተል የቆየችው ሙሉ ሲሳይ በነፃ እንድትሰናበት ተደርጓል።
ተከሳሾች  ከመጪው ሰኔ 17 እስከ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተከታታይ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት እንዲያቀርቡም መታዘዛቸውን ጋዜጣው ዘገባውን አጠቃሏዋል። ዘመነ ካሴ የተከሰሰው በሌለበት ነው::

No comments:

Post a Comment