Thursday, May 29, 2014

ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ቤቶች በዶዘር እየፈረሱ ነው

በዛሬው ዕለት ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ ህገ ወጥ ናቸው የተባሉ ቤቶች በዶዘር እየፈረሱ እንደሚገኙ ከቦታው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡ በተለይ ቦሌ እየተባለ የሚጠራው ሰፈር የሚገኙ ቤቶች በዛሬው ዕለት እየፈረሰ እንደሚገኝና ህዝብ ይቃወማል በሚል ቡችሌ፣ ሚሊሻ፣ ህዝባዊና ልዩ ፖሊስ ከፍተኛ ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይህ ቦሌ ተብሎ የሚጠራው ሰፈር ትናንት ሊፈርስ የነበረ ቢሆንም በግንቦት 20 ምክንያት እንደታለፈ ተገልጾአል፡፡
ደብረ ማርቆስ ውስጥ ቤቶችን ማፍረስ የተጀመረው ግንቦት 18ና 19/2006 ዓ.ም ሲሆን ቀበሌ አራት (4) በተለይም ሞንቃ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር 400 ያህል ቤቶች እንደፈረሱ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ቦሌ የተባለው ሰፈር እንዳይፈርስ በተደረገበት በትናንትናው ቀን ከ23 አመት በላይ ግብር ሲከፈልበት የኖረ የአንድ ግለሰብ ቤት መፍረሱም ታውቋል፡፡ አፍራሽ ግብረሃይሉ የቤቱን ጣራ ካፈረሰ በኋላ ግለሰቡ ለ23 ዓመት ግብር ሲከፍልበት የነበረ መሆኑን በመገለጹ ግድግዳው ብቻ እንደቆመ ወደ አቤቱታ መመራቱን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ውስጥ አብዛኛዎቹ ቤቶች ከ1997 ጀምሮ የተሰሩ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ቤቶች አርሶ አደሮች በአሁኑ ወቅት ወደ ከተማ በተከለለው መሬታቸው ላይ የሰሯቸው እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ‹‹የአርሶ አደሮቹ መሬቶች ወደ ከተማ ሲከለሉ መንግስት ተለዋጭ ወይንም ካሳ የመስጠት ግዴት የነበረበት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥነት እያፈረሰ እያፈረሰ ይገኛል›› ያሉት አንድ የከተማዋ ነዋሪ እርምጃው ህገ ወጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡



No comments:

Post a Comment