Friday, May 25, 2018

የነ አቶ መላኩ ፈንታ ክስ ተቋረጠ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 17/2010)አቶ መላኩ ፈንታና ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ በሌብነት ወንጀል የተከሰሱ ታዋቂ ባለሀብቶች ክሳቸው መቋረጡን ፋና ዘገበ።
የእነ እቶ መላኩ ክስ መቋረጥ የሕወሃት ንብረት በሆነው ፋና በሮድካስቲንግ በይፋ ከተዘገበ በኋላ ዜናው ከድረገጹ እንዲነሳ መደረጉ ታውቋል።
ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ክሳቸው እንዲቋረጥ አቃቤ ህግ ጠየቀ ሲል ሌላ ዘገባ አቅርቧል።
በሌብነት ወንጀል ተከሰው የነበሩት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ እና የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ክሳቸው መቋረጡን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል።

ከሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪም አቶ ነጋ ገብረእግዚአብሔር ፣ አቶ ከተማ ከበደ፣ አቶ ጌቱ ገለቴ፣ አቶ ገብረስላሴ ገብሬ፣ ኮሎኔል ሀይማኖት ተስፋው፣ አቶ ገምሹ በየነ፣ ጂ ኤች ሲ ኔክስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ጌታስ ኩባንያ፣ ኮሜት፣ ነፃ ትሬዲንግ እና ፍፁም ገብረመድህን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያም ክሳቸው ተቋርጧል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በሌብነት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ አቶ ዋሲሁን አባተ፣ አቶ አክሎክ ደምሴ፣ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል፣ አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ ወይዘሮ ሰኸን ጎበና፣ አቶ ጌታቸው ነገሪ፣ አቶ ነጋ መንግስቱ እና አቶ ሙሳ መሀመድም ከዛሬ ጀምሮ አቃቤ ህግ ክሳቸውን እንዳቋረጠና ዛሬውኑ ከማረሚያ ቤት እንደሚወጡ በዝገባው ተመልክቷል ።
በሌብነት ወንጀል እጅ ከፍንጅ የተያዙትን አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ፥ ባለሃብቱ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሄር እንዲሁም በግዙፍ ጨረታዎች ሙስና የሚታሙት የቀድሞው መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑ ሕወሐት የፖለቲካ እስረኞች ሲለቀቁ እንደ ቅድመ ሁኔታ መደራደሪያ አድርጎት ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይገምታሉ።
በሽብር ወንጀል የተከሰሱ የተለያዩ ግለሰቦችም ክሳቸው ተቋርጧል እየተባለ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም የእነ እቶ መላኩ ክስ መቋረጥ የሕወሃት ንብረት በሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ በይፋ ከተዘገበ በኋላ ዜናው ከድረገጹ እንዲነሳ መደረጉ ነው የታወቀው።
ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ይህው ጣቢያ ክሳቸው እንዲቋረጥ አቃቤ ህግ ጠየቀ ሲል ሌላ ዘገባ አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment