Friday, May 25, 2018

ከ900 በላይ የአማራ ተወላጆች ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 17/2010) ከኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ደጋ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ900 በላይ የአማራ ተወላጆች ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸው ተገለጸ።
ተፈናቃዮቹ በአማራና ኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ትብብር በወልዲያና በጭፍራ መካከል በሚገኝ ሃሮ ተብሎ በሚጠራ በረሃ ላይ ሰፍረው የሚገኙ ሲሆን ወደ ሌላ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱም በመከላከያ ሰራዊት እየተጠበቁ መሆናቸውም ተገልጿል።
አካባቢው ደረቅ መሆኑና ውሃ ማግኘት አለመቻሉ ህጻናት ለበሽታ እየተጋለጡ መሆናቸውን ከስፈራው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ተፈናቃዮቹ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በ1972 በሰፈራ ወደ አካባቢው መሄዳቸውን ይናግራሉ ።
በሰፈሩበት አካባቢም ለዘመናት መኖራቸውንና ሃብት ንብረት አፍርተው በሰላም ይኖሩ እንደነበር በስፍራው ተግኝቶ ለነበረው ታዛቢ ቡድን ተናግራዋል ።
መሬቱ የእናንተ አይደለም ልቀቁና ሄዱ ተብለው አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውንም ይናገራሉ።
በኢሉባቡር የአማራ ተወላጆችን ማፈናቀሉ በአምስት ወረዳዎች የተከሰተ ሲሆን የቡኖ በደሌ ግን የከፋ እንደሆነ ተገልጿል።
ተፈናቃዮቹ በፖሊስ ታስረው ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 9/2010 የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ባለስልጣናት በመተባበር አሁን ወደሚገኙበት በወልዲያና ጭሮ መካከል በሚገኘው ሃሮ በረሃ ላይ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል።

ተፈናቃዮቹ ለታዛቢዎቹ እንደተናገሩት አሁን ወዳሉበት ቦታ በሰፈሩበት ወቅት ከተደረገላቸው ሶስት ኪሎ እህል ድጋፍ ውጪ እስካሁን ማንም እንዳላያቸውና እንዳላናገራቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አካባቢው ደረቅ በመሆኑ ውሀ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ገጥሞናል ይላሉ። ተንቀሳቅሰን እንዳንፈልግ እንኳን በመከላከያ ሰራዊት ተከበናል ይላሉ።
በተለይም ሕጻናት በመኖራቸው በውሀ እጥረት ለከፍተኛ ስቃይ መዳርጋቸውንና ለበሽታም እየተጋለጡ መሆኑን ታዛቢዎቹ ለኢሳት ተናግራዋል።
እንደታዛቢዎቹ ከሆነ የህጻናቱንና የወጣቶቹ ችግር የበለጠ የከፋ ያደረገው ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ ከኦሮምኛ ቋዋንቋ ውጪ መስማትም ሆነ መናገር ባለመቻላቸው ችግሮቻቸውን ማስረዳት መቸገራቸውንም ገልጸዋል።
ወደቀድሞ ቦታቸው እንዳይመልሱም የመሬት ሽንሸና በመካሄዱ ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ተገልጿል።
ኢሳት በተደጋጋሚ እንደዘገበው በተለያዩ ከልሎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ለዘመናት ከሚኖሩበት አካባቢ ወደ ክልላችሁ ሂዱ በሚል ሰበብ ሀብት ንብረታቸውን ተቀምተው በመፈናቀል ላይ ናቸው።
በቅርቡ ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ታወላጆች ባህርዳር ከተማ የሚገኙ ሲሆን ከፌደራልም ሆነ ከክልሉ መንግስት ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳያገኙ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment