Wednesday, May 2, 2018

አቶ አብዲ ኢሌ “ ኦሮሞዎች ጠላቶቻችን ናቸው” ሲሉ ፈረጁ

(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ/ም) የኢትዮ-ሶማሊ ክልል መሪ አቶ አብዲ ኢሌ “ ኦሮሞዎች ጠላቶቻችን ናቸው” ሲል በጅጅጋ ከተማ ለአስቸኳይ ስብሰባ ለተጠሩ ለክልሉ ሽማግሌዎች ተናግረዋል። በከፍተኛ የስሜት መረበሽ ውስጥ ሆነው ንግግር ያደረጉት አቶ አብዲ “ ዶ/ር አብይ እና ሌሎች ወደ ጅግጅጋ መጥተው የነበሩት ኦሮሞዎች ውሸታሞች ናቸው” ብለዋቸዋል። “በእኛ ላይ ስውር ጦርነት ከፍተውብናል” የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ “ከኦሮሞዎች ጋር ለመዋጋት ዝግጅት ማድረግ አለብን” ሲሉ አክለዋል። “በአንድ በኩል ለሰላም ዝግጁ ነን ይላሉ፣ በሌላ በኩል በክልሉ መንግስትና ህዝብ ላይ ጦርነት ለማወጅ በስውር ያሴራሉ” የሚሉት አቶ አብዲ ኢሌ ፣ የዶ/ር አብይን መንግስት እንደማያምኑትና የክልሉ ህዝብም ድጋፉን እንዳይሰጣቸው ጠይቀዋል። በቅርቡ እርሳቸውን በመቃወም በክልሉ የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች የሴራው አካል ማሳያ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ አብዲ፣ ህዝቡ በብዛት ወደ አደባባይ እየወጣ ለክልሉ መንግስት ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል። እንደ ኦሮሞወች ሁሉ የሶማሊ ቄሮዎች መፈጠር እንዳለባቸውና ክልሉም በዚህ መንገድ የሶማሊ ቄሮዎችን እንዲያደራጅ አቶ አብዲ ለወረዳ አመራሮች ትእዛዝ እንደሚሰጡ
በንግግራቸው ፍንጭ ሰጥተዋል። ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ጅቡቲ ተጉዘው ከአገሪቱ መንግስት ጋር መነጋገራቸው ለአቶ አብዲ የሚዋጥ አልሆነም። ኢሳዎች ከኦነጎች ጋር ስምምነት ማድረጋቸው ካህዲናታቸውን ያሳያል የሚሉት አቶ አብዲ ኢሌ ፣ በኦጋዴኖች ላይ ጠቃት ለመፈጸምና “ ነዳጃችንን ጨምሮ የክልሉን ሃብት ለመዝረፍ መሰናዶ ጨርሰዋል” ብለዋል።፣ ኦጋዴዎች ለመብታቸው እንዲነሱም ተማጽነዋል።“ እነ ለማና አብይ በውጭ ከሚኖሩት ኦነጎች ጋር እየተነጋገሩ ጉዳያቸውን ሲያስፈጽሙ እኔስ ከኦብነግ ጋር ብነጋገር ማን ይከለክለኛል?” የሚሉት አቶ አብዲ ኢሌ፣ “ ዛሬ ኢሳዎች ኦጋዴንን ከምድር ላይ ለማጥፋት ከኦነግ ጋር እየመከሩብን ነው፤ እኔ ነበርኩኝ ሰዎች ያደረኩዋቸው፣ እነሱ ግን ካዱኝ “ በማለት በምሬት ተናግረዋል። በቅርቡ በሽንሌ ዞን የተነሳው ተቃውሞ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ከተዛመተ በሁዋላ፣ በድሬዳዋ የአብዲ ኢሌ ተቀናቃኝ ተደርገው የሚታዩት የአቶ አህመድ ጣሂር አዴ ቤት እንዲሰበርና ብርበራ እንዲካሄድ ያደረጉት የምስራቅ እዝ አባል የሆኑት ኮሎኔል ተክላይ እና ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው እንዲታሰሩ መደረጉ፣ አቶ አብዲ ኢሌን በእጅጉ አስደንግጧል። የአቶ አብዲ ንዴትና ዛቻ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። አቶ አብዲ ኢሌ የኢትዮ-ሶማሊ ክልል ህዝብ አማራና ኦሮሞን እንዳይግፍና ከትግራይ ህዝብ ጎን እንዲቆም መጠየቃቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ ኢሳት መልቀቁ ይታወሳል። የኦሮምያ ክልል መንግስት በአቶ አብዲ ለቀረበበት ውንጀላ እስካሁን በይፋ የሰጠው መልስ የለም። አቶ አብዲ ኢሌ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የኦሮሞ ተወላጆች ከኢትዮ-ሶማሊ ክልል እንዲፈናቀሉ ቢያደርጉም እስካሁን በህግ ተጠያቂ አልሆነም። ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበት ወቅት የኦሮምያ ክልል መሪ የሆኑትን አቶ ለማ መገርሳንና አቶ አብዲ ኢሌን እጅ ለእጅ በማያያዝ እርቀ ሰላም እንደወረደ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች በሁለቱ ክልሎች መካከል ሌላ ደም አፋሳሽ ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አጭረዋል።

No comments:

Post a Comment